ቀጥታ፡

ሀገሪቱ አሁን ያጋጠማትን ችግር እንደ አድዋ ድል በመተባበር ሊፈታ እንደሚችል ተገለጸ

ሀዋሳ፣ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው አድዋ ላይ ድል እንዳደረጉ ሁሉ ሀገሪቱ አሁን ያጋጠማት ችግርንም በመተባበር መፍታት እንደሚቻል የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎች ገለጹ።

124ኛው የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተማሪዎች እንዳሉት ቀደምት አባቶች ያጠናከሩት የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠል ይገባል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አወቀ ሀምዛዬ በሰጡት አስተያየት ጀግኖች አባቶች ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር ድል የነሱበት ወቅት የአለም ኃያላን መንግስታት በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ መላው አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ተስማምተው ነበር።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ  ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ በአንድ በኩል በአፄ ቴዎድሮስ የተጀመረውን አንዲት ታላቅ ሀገር የመመስረት ራዕይ ለማሳካት በሌላ በኩል ደግሞ ከየአቅጣጫው የሚመጡ የውጭ ጫናዎችን ለመመከትና ሉአላዊነትን  በማስከበር ውጥረት ውስጥ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

ከጦርነቱ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ረሀብም እንደዚሁ ሀገሬውን የፈተነበት ጊዜም እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ የነበሩባቸውን ፈተናዎች በመቋቋም ተባብረው ወራሪውን የኢጣልያ ጦር ድል በማድረግ ሉአላዊነታቸውን አስከብረዋል።

እንደ ዶክተር አወቀ ገለጻ  የውስጥ ችግሮቻቸውን በመፍታት አንዲት ጠንካራ ሀገር መመሥረት ችለዋል፡፡

የአድዋ ድል ለአሁኑ ትውልድ ተባብሮ በመስራት ችግሮችን ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸው

 "በቁርጠኝነት ተባብረን ከሰራን አሁን ላይ እንደ ሀገር የገጠሙንን ችግር መፍታት እንችላለን " ብለዋል፡፡


በዩኒቨርሲቲው የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን  ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው ጀግኖች አባቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት ያሳዩት ተጋድሎ ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ስንቅ እንደሆነ ገልፀው ለአንድነትና ለሀገር ግንባታ ትልቅ ሚና ያለው ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታሪክ የራሱ ጠንካራና ደካማ ጎን ያለው በመሆኑ ከዚህ በመማር መልካም ሥራዎችን ይበልጥ አጎልብቶ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመው "የአድዋ ድል አንድነትን፣ ጥንካሬንና መተባበርን የተማርንበት ታሪካችን ነው" ብለዋል፡፡ 

"የአድዋ ድል እኛ ኢትዮጵያውያን ለመላው አፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የሆንበት ነው "ያለው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው  የአንደኛ ዓመት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ኃይለሚካኤል አበራ ነው።

"ከታሪካችን ተምረን ጥሩ ነገሮችን ማስቀጠል ይገባናል "ያለው ተማሪ ኃይለሚካኤል ቀደምት አባቶች ያጠናከሩት የኢትዮጵያን አንድነት በማስቀጠል  ሀገሪቱ አሁን የገጠማትን ችግር መፍታት እንደሚቻል ገልጿል።

የአራተኛ ዓመት የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ የአዳምጥላ በቀለ በበኩሏ የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን  ወደ ጎን በመተው በአንድነት ሆነው ያስመዘገቡት ድል  መሆኑን ተናግራለች፡፡

ጀግኖች አባቶች ያሉባቸው የውስጥ ችግሮች በመቋቋም ማሸነፍ የቻሉት በመተባበራቸው እንደሆነ ገልጻ

"ሁላችንም አንድ ብንሆን  ችግሮችን  ማለፍ እንችላለን"  ብላለች ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም