የኢትዮጵያ የወደብና ሎጂስቲክስ ወጭዋን ለመቀነስ እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የወደብና ሎጂስቲክስ ወጭዋን ለመቀነስ እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የወደብና የሎጂስቲክስ ክፍያ ወጭዋን ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች መሆኑን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሀመድ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነውን የወጪና የገቢ ንግዷን የምታከናውነው በጅቡቲ ወደብ በኩል መሆኑ ይታወቃል።
ይህም ከፍተኛ የሆነ የወደብና የሎጂስቲክስ ክፍያ ሲሆን ውጤታማና ቀልጣፋ አሰራር የተዘረጋለት አሰራር መሆኑ ይገለፃል።
በጅቡቲ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሀመድ ኤምባሲው በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል የሚረዱ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሰራሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያረጋገጠ ሆኖ የጅቡቲን የአሰራር ሕግ ጠብቆ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዓመታት በፊት የሙስና፣ አላስፈላጊ የዲሜሬጅ ወጪ እንዲሁም ረጅም ጊዜ ወደብ ላይ እቃ የማቆየት ችግሮች እንደነበሩ አምባሳደሩ አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ግን የትራንስፖርት አቅርቦት፣ የመንገድ ደህንነት፣ የነዳጅ እንቅስቃሴና የባቡር ጭነት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች መመቻቸታቸው አገልግሎቱ የተሳለጠ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።
ለዚህም ከትራንስፖርት ማህበራት፣ ከጅቡቲ መንግስትና ከወደብ አስተዳዳሪዎች ጋር ቋሚ የመገናኛና የመወያያ መድረኮች ተፈጥረዋል ነው ያሉት።
እንደ አምባሳደሩ ገለፃ አሁን ላይ በመጠኑም ቢሆን የዘርፉን ወጪ መቀነስና አሰራሩንም ማቀላጠፍ መቻሉን ተናግረዋል።
ጥብቅ ክትትል እየተደረገ በመሆኑ በቀን እስከ 500 የሚደርሱ የነዳጅ ቦቴዎችም ምንም ችግር ሳይገጥማቸው በትክክለኛው ሰዓት በመድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የአፈር ማዳበሪያ፣ ስንዴና ስኳር እንዲሁም ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችና ሸቀጦች በተቀላጠፈ አሰራር እየተከናወኑ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ሆኖም አሁንም ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እልባት ያላገኙ የተለያዩ ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውን አምባሳደር አብዱልአዚዝ ገልጸዋል።
ከዲኪል ጋላፊ የሚዘልቀውና ከፍተኛ መጨናነቅ ያለበት አስፋልት ከ120 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነው በመበላሸቱ ጫና ፈጥሯል ብለዋል።
የባቡር ትራንስፖርቱም የታሰበውን ያህል ውጤታማ ባለመሆኑ እቃዎችን በፍጥነት ከወደብ ላይ ማንሳት አለመቻሉ ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።
አልፎ አልፎ የኮሪደር ጠባቂዎች የሚፈጥሯቸው ችግሮችና አንዳንድ አሽከርካሪዎችም የተከለከሉ ነገሮችን ይዘው መገኘት እክል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።