ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ የተቀናጀ ጥረት መቀጠል አለበት

ድሬዳዋ፣ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር የገጠሩን ህብረተሰብ ህይወት ለመለወጥ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቆመ።

 በግብርና ዕድገት ምዕራፍ ሁለተኛ  መርሃግብር አተገባበር ላይ የሚሳተፉና የሚገመግሙ የግብርና ልማት አማካሪ ምክር ቤት ውይይት በድሬደዋ ተካሄዷል፡፡ 

በግብርና ሚኒስቴር የልማት አካላት  ዳይሬክተሩ አቶ ታደሰ ጭርፋ በውይይቱ ወቅት  እንደተናገሩት ምክር ቤቱ የምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የግብርና ባለሙያዎችና የገጠሩ ነዋሪዎች ፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ አስር ተቋማት የተካተቱበት ነው።

"ምክር ቤቱ በግብርና ዕድገት ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት የገጠሩን ኑሮ እንዲሻሻል አግዟል" ብለዋል፡፡

ይህ አበረታች ጅምር  ከአርሶ አደሩ ጋር ይበልጥ በመቀራረብ   የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ የተቀናጀ ጥረት መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ምክር ቤት በአስተዳደሩ ተገንብተው ከተቀመጡ የገበሬ ማሰልጠኛ ተቋማት አራቱን ወደ ሥራ በማስገባት ለአርሶ አደር  የአቅም ግንባታ፣ የቁሳቁስና የምርጥ ዘር አቅርቦት በቀላሉ እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በተለይ የፈዲስ የምርምር ማዕከልና የሀረማያ ዩኒቨርስቲ  ከድሬዳዋ ቆላማ አየር ንብረትና አነስተኛ ዝናብ ጋር የሚዋሃዱና ከነባር ምርቶቹ በአስር እጥፍ ብልጫ ያለው ምርት የሚሰጡ  የማሽላና የበቆሎ ዘሮችን ተደራሽ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

"አርሶ አደሩም የተባዙ ምርጥ ዘሮችን በመጠቀምና ምርቱን በማሳደግ ኑሮውን እያሻሻለ ይገኛል፤ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግም አግዟል" ብለዋል፡፡

ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን፣ ለሀረሪ ክልልና ለድሬዳዋ አስተዳደር በምርምር የተገኙና የተሻሻሉ ሁለት ዓይነት ምርጥ ዘሮችን በማከፋፈልና  ሥልጠና በመስጠት የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፈዲስ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ አቶ አለማየሁ ብሬ ናቸው፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በግብርና ዕድገት መርሃ ግብር ዝናብ አጠር ለሆኑ የድሬዳዋ አስተዳደር 16 ገጠር ቀበሌዎች በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የማሽላና የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን በማሰራጨት የተሻለ ውጤት ማምጣት መቻሉን አመልክተዋል፡፡

"የማሽላ ምርጥ ዘር በመጠቀም በሄክታር ከ30 እስከ 45 ኩንታል ማግኘት ተጀምሯል፤ ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ ቀደም ሲል በሄክታር ያገኝ ከነበረው አምስት ኩንታል አንጻር ከፍተኛ ልዩነት አምጥተናል " ሲሉ ጠቅሰዋል።

በቀጣይም  ትህንን ከማጠናከሩ በተጓዳኝ  የምርምር ድግግሞሽ እንዳይኖር ከሀረማያ ዩኒቨርስቲ ጋር በመናበብ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የዱጁማ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር አደም ዩያ  በሰጡት አስተያየት ምርጥ ዘር መጠቀም መጀመራቸው ቀደም ሲል በስድስት ራት ይደርሱ የነበሩት የማሽላና የበቆሎ ምርቶችን በሶስት ወራት እየሰበሰቡ መሆናቸው  ተናግረዋል፡፡

" ምርቱም በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ አለው ፤ ሁሉም አርሶ አደር እንደኔ ተጠቃሚ እንዲሆን ዘሩን በስፋት ማዳረስና ማሳወቅ ይገባል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም