ኮሚሽነሩ ወንጀልን ለመከላከል ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል አሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽነሩ ወንጀልን ለመከላከል ፖሊስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል አሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) የወንጀል ክስተቶችን ለመከላከል በየደረጃው የሚገኝ የፖሊስ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው አሳሰቡ።
በሰመራ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ ተጠናቋል።
ጉባኤው ሲጠናቀቅ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራሉ እንደገለጹት መንግስት በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከመታገሱ ጋር ተያይዞ በየደረጃው የሚገኘው የፖሊስ ኃይል ህግ የማስከበር ክፍተቶች ተስተውለውበታል።
በዚህም ንጹሃን ዜጎች እየተጎዱና ሰላማቸውም እየታወከ ንብረትም መጥፋቱን አመልክተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ የወንጀል ክስተት የመለየት ስራ ሲካሄድ መቆየቱን አስረድተዋል።
የኃይማኖትና ብሄር ግጭቶች፣ የኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች በተለያዩ አካባቢዎች የፈላጭ ቆራጭነት ሚና፣ የገጠርና ከተማ ሽፋታና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ እንዲሁም ሚዛናዊነት የጎደላቸው የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ከተለዩት ውስጥ ጠቅሰዋል።
እነዚህ ወንጀሎች እንዳይደገሙ ለመከላከል የፌዴራል ፖሊስን እገዛ ግድ ከሚልባቸው ውጭ ክልሎች በራሳቸው አቅም ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባትና ህግ የማስከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በየደረጃው የሚገኘው የፖሊስ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅና ወንጀልን ለመከላከል ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጸጥታ ኃይሉ ለሰላም እሴት ግንባታና ግጭት መከላከል ላይ አጋዥ ከሆኑ የማህበረሰብ አደረጃጀቶችና የኃይማኖት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ አገልጋይነት ስብእና የተላበሰና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የወንጀል መከላከል ስራ ማከናወን እንዲቻል ተከታታይ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አሊዲሊ አለሳ የጋራ መድረኩ ለቀጣይ ወንጀል መከላከል ስራዎች አጋዥ የሆኑ ተሞክሮዎች የተለዋወጡበትና እርስ በርስም መቀራረብ የተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሉ አብሮ የመስራት፣ የህብረተሰቡን ደህንነትና ሰላም የማስከበር ሚናውን ለመወጣት የሚያግዙ ምክክሮችና መቀራረቦች የተመቻቸበት መድረክ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ናቸው።
የፌዴራል፣ የዘጠኙ ክልላችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት ጉባኤው ባለስድስት ነጥብ የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት ነው ትናንት የተጠናቀቀው።