ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ በከሚሴ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ በከሚሴ ተከፈተ
ደሴ፣ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ 11ኛውን ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ በከሚሴ ከፈተ።
ቅርንጫፉ በተከፈተበት ስነስርዓት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው እንደገለጹት ባንኩ በተለያዩ አካባቢዎች ከወለድ ነጻ ብቻ አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎችን አመቻችቷል።
ይህ ቅርንጫፍም "ሙፍቲ ዳውድ" በሚል ስያሜ ነው የተከፈተው ።
ከወለድ ነጻ ከሚጠቀሙ አንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ደንበኞች ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀስ እንደተቻለ ጠቁመው፤ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱንም አመልክተዋል።
የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግም የቅርንጫፎችን መጠን በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 26 ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሐሰን አካባቢው የእስልምና እምነት ተከታይ ስለሚበዛበትና ወለድ ስለማይፈልግ ብዙ ጊዜ ገንዘቡን ከቤት እያስቀመጠ ለስርቆትና ለሌላም ችግር ይጋለጥ እንደነበረ ገልጸዋል።
ባንኩ ቅርንጫፉን እዚህ መክፈቱ ህብረተሰቡን ከመሰል ስጋቶች ታድጉታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው ቅርንጫፎቹ መከፈታቸው ሁሉን አሳታፊ ከመሆኑም ባለፈ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡም የካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለባንኮቹ አስፈላጊውን ከለላ ማድረግ እንደሚገባውም አመልክተዋል።
የከሚሴ ከተማ ነዋሪ ሸህ መሃመድ ሰይድ እንደተናገሩት በከተማው ከወለድ ነጻ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ መከፈቱ ሲፈልጉት የነበረ ነው።
በዚህ መደሰታቸውንና አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል።
በመክፈቻው ስነስርዓት ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ ኡለማዎችና፣ የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች እና የመንግስት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ከ6 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትና ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ማፍራቱም ተመልክቷል።