ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር አንፃራዊ ስፖርታዊ ጨዋነት ታይቶበታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር አንፃራዊ ስፖርታዊ ጨዋነት ታይቶበታል
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2012 የመጀመሪያ ዙር ውድድር ካለፉት ጊዜያት በተሻለ አንጻራዊ ስፖርታዊ ጨዋነት የተስተዋለበት እንደነበር ተገለጸ።
የሊጉ የመጀመሪያ ዙር ወድድር ከህዳር 28 እስከ የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ የመጀመሪያውን ዙር የውድድር ሂደት አስመልክቶ ግምገማ አካሂዷል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንደገለጹት፤ የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ መልኩ አንጻራዊ ስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት ነው።
ይህ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውድድሮች እየታየ ያለ አንጻራዊ ሰላም ተሻሽሎ እንዲቀጥል በስፖርቱ ዙሪያ ያሉ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
አቶ ኢሳያስ ሠላማዊ የውድድር መንፈሱ በዘላቂነት እንዲቀጥል ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር መስራት ይገባልም ብለዋል።
የፕሪሚየር ሊጉ የሊግ ካምፓኒ መቋቋሙን እንደ መልካም አጋጣሚ ጠቅሰው፤ ክለቦች በተገቢው መንገድ ህጋዊ እውቅና ይዘው እንዲደራጁ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሊግ ካምፓኒው በተደራጀ አግባብ ወደ ስራ ሲገባም ክለቦች የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ተተኪ ወጣት ተጨዋቾችን ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሊግ ካምፓኒ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በበኩላቸው የሊግ ካምፓኒው ውድድሮችን መምራት ብቻ ሳይሆን እግር ኳሱ ከመንግስት በጀት ድጎማ ተላቆ የራሱን ገቢ ማመንጨት እንዲችል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከአሁን በፊት ይፋዊ ዓርማ ያልነበረው ፕሪሚየር ሊግ አዲስ መለያ /ሎጎ/ አግኝቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወጥ የሆነና በየውድድር ዓመቱ የማይቀያየር ዋንጫ እንዲኖረውም የዋንጫ ዲዛይን ለማሰራት ኮሚቴው በቅርቡ ጨረታ እንደሚያወጣም ተገልጿል።
የክለቦች ደጋፊ ማህበራትና አመራሮች ለስፖርታዊ ጨዋነት በሰጡት ትልቅ ትኩረት የተካሄዱት አብዛኞቹ ውድድሮች ስፖርታዊ ጨዋነት የተስተዋለባቸው እንደነበሩም አንስተዋል።
በሁለተኛ ዙር የሊጉ ቀሪ የውድድር ዘመንም ይህንኑ አንፃራዊ ሠላም መቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብርሃቱም የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ወደ ክለቦቻቸው ሲመለሱ የሠላም አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ ሃላፊነት ሰጥተን ነው የምንልካቸው ብለዋል።
የሊግ ካምፓኒው ውጤታማ እንዲሆንም ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው እንደ ኳታርና ሌሎች የእስያ አገራት ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የውድድር ዘመን 120 ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን ከ1 ሚሊዮን 650 ሺህ 200 በላይ ደጋፊዎች ስታዲየም ገብተው ጨዋታዎቹን ተመልክተዋል።
በዙሩ ውድድር የክለብ ደጋፊዎችና አመራሮች ለስፖርታዊ ጨዋነት ትኩረት ሰጥተው መስራት፣ የዳኝነት ውሳኔን በፀጋ መቀበል፣ በደጋፊዎች መካከል መቀራረብ መፈጠሩ፣ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን መኖሩ፣ የክለብ ደንብ አስከባሪዎች ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር መስራት፣ ወጥ የጨዋታ ፕሮግራም መካሄድ የሚሉት ከጠንካራ ጎኖች መካከል ተጠቅሰዋል።
ውድድሮች በታቀደላቸው ቀናት አለመጀመር፣ ጥቂት የሚባሉ ደጋፊዎች የዳኞችና ተጫዋቾችን ስም በመጥራት መሳደብ፣ የታሸገ ውሃ፣ ድንጋይና ሳንቲም መወርወር፣ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ቅስቀሳዎች፣ ሙዚቃዎች፣ ባነሮችና መፈክሮች መታየት፣ ጥቂት ደጋፊና ተጫዋቾች የዳኛን ውሳኔ በፀጋ አለመቀበልና በአንዳንድ ቦታዎች ለተጋጣሚ ቡድኖች አስፈላጊውን መስተንግዶ አለማድረግ በውድድሩ ከታዩ ክፍተቶች መካከል ናቸው።
ለመፈጸም ከታቀዱ መካከልም የክለቦችን ሜዳ አስተካክሎ ለውድድር ዝግጁ ማድረግ፣ ለጨዋታ ታዛቢ ኮሚሽነሮች በየስታዲሞች ግልፅ ቦታ ማዘጋጀት፣ ከክለቦች ዓርማ በቀር ምንም አይነት የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ነገሮች ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ ማድረግና ከዳኞች ኮሚቴ ጋር ተናቦ መስራት የሚሉት ይገኙበታሉ።
በግምገማው ላይ የፌዴሬሽን አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪዎች፣ የክለቦች ስራ አስኪያጆችና የደጋፊ ማኅበራት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።