የህዳሴ ግድብና ኢትዮጵያዊነትን የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብና ኢትዮጵያዊነትን የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ)የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ኢትዮጵያዊነትን በአንድ ጭብጥ ያጣመረ ከ40 በላይ ታዋቂ አርቲስቶች የሚሳተፉበት የዘጋቢ ፊልም ቀረፃ ተጀመረ።
ሙ ላይ ከ40 በላይ ስመ ጥር አርቲስቶችና የተለያየ አኗኗርና ባህል ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስለ ግድቡና ስለ አገር አንድነት ያላቸውን ሃሳብ በነፃነት ይገልፁበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የአርቲስቶቹ ቡድን የአባይን ገባሮች መሰረት አድርጎ የኢትዮጵያን ባህል ከአባይ ግድብ ጋር እንዲሁም ከአገራዊ አንድነት አንፃር እየቃኘ እስከ ግድቡ የሚዘልቅ ዘጋቢ ፊልም ለመቅረጽ ተሰማርቷል።
ቀረፃው እየተካሄደ ያለው የማህበረሱን አኗኗርና ለግድብ ያላቸውን ተሳትፎ በሚያሳይ መልኩ በሚኖሩበት ቦታ ላይ መሆኑን የፕሮግራሙ አስተባባሪ አርቲስት አንድነት አያሌው ለኢዜአ ተናግሯል።
“የአባይ ገባሮች ተስማምተው በአንድ ላይ በመፍሰሳቸው ታላቅ ሆነዋል፣ለአገራትም ጠቅመዋል፣በዓለምም ተፅዕኖ እንደፈጠሩ ሁሉ ኢትዮጵያዊያንም አንድ ሆነን ለጋራ ዓላማ መስራት አለብን” ነው ያለው።
ፊልሙን አርቲስቶቹ በራሳቸው ተነሳሽነት የሚሰሩት ሲሆን ለፊልሙ መስሪያ የሚወጣውን ወጪም ከራሳቸውና ከስፖንሰር የተገኘ እንዲሁም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት በተገኘ የቁሳቁስ ድጋፍ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ ፊልሙ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዘጠነኛ ዓመት በሚከበርበት መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓም ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ሃሳቡ በአርቲስት ማክዳ አፈወርቅ ተጠንስሶ ወደ ተግባር መቀየሩንና ሲያልቅም በነፃ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት እንደሚሰጥም ታውቋል።