ቀጥታ፡

የዕምነበረድ ዘርፍ መሳሪያዎችና ቴክሎጂዎችን የሚያንቀሳቅስ የባለሙያ እጥረት አለ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ)  በዕምነበረድ ዘርፍ መሳሪያዎችና ቴክሎጂዎችን የሚያንቀሳቅስ በመስኩ የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት መኖሩ ተገለጸ። 

የዕምነበረድ ዘርፉ የሚመራበት ስትራቴጂ ሊቀረጽ እንደሚገባም ተገልጿል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከኢጣሊያ የንግድ ኤጀንሲ ጋር በመተባባር ኢትዮጵያ በዕምነበረድ ሀብቷ ተጠቃሚ በምትሆንበት ሁኔታ ላይ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

ኢትዮጵያ የዕምነበረድ ሀብትን ለተለያዩ አገልግሎቶች መጠቀም የጀመረችው በቀደምት ዘመናት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች የዕምነበረድ ሀብት የሚገኝባቸው ዋነኛ አካባቢዎች ሲሆኑ ሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ የዘርፉ እምቅ ሀብት እንዳላቸው ይታወቃል።

ነገር ግን አገሪቷ ይህን እምቅ ሃብት እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ የዘርፉ ተዋናዮቹ ሲገልጹ ይደመጣል።

የአርዲ ዕምነበረድ ፋብሪካ ባለቤትና ኃላፊ አቶ ገነነ ነጋሽ፤ በኢትዮጵያ ዘርፉ የሚያስፈልጉትን መሳሪያዎች ተረድቶ ማንቀሳቅስ የሚችል የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ስለመኖሩ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ ለዕምነበረድ ያለው ግንዛቤና ትኩረት ዝቅተኛ እንደሆነና የሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ዕምነበረድን በተሻለ መልኩ መጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል ተሾመ በበኩላቸው በአገሪቷ ያለውን ሀብት ለመጠቀም ዘርፉ የሚመራበት ስትራቴጂ መቅረጽ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዕምነበረድ አምራቾች የሚቀርበውን የመጨረሻ ምርት በሚፈለገው ልኬት የመቁረጥና ለስራ በተገቢው መንገድ የማቅረብ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ይህ ደግሞ የዕምነበረድ የመጨረሻ የምርት ሂደቶች ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ባለመኖራቸው በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

በውይይቱ ወቅት የዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦትም ማደግ እንዳለበት ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረቱን ለመፍታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ለመክፈት ታቅዷል ብለዋል።

ተቋሙን የመክፈቱ ስራ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ በዘርፉ የተሰማሩ ሰራተኞችን ክህሎት ማሻሻልና ከሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራበት ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል።

የዕምነበረድ ዘርፉ የሚመራበት ስትራቴጂ ለማዘጋጀት ከባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ግብዓት ለማሰባሰብ ማቀዱንም ጠቅሰዋል።

የኢጣሊያ የንግድ ድርጅት የአዲስ አበባ ቢሮ የንግድ ኮሚሽነር ሚስ ሲሞና አቶሪ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል በመጠቀም አገሪቷ ከዕምነበረድ ሀብቷ የምታገኝውን ጥቅም ማሳደግ ትችላለች ብለዋል።

የአገራቸው መንግስት የዕምነበረድ አጠቃቀም ላይ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለማቃለል ለሚቋቋመው ተቋም ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዕምነበረድ ሀብቷን የምታስተዋውቅበት ሙዚየም እንዲገነባና ከዘርፉም ተጠቃሚ እንድትሆን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም