ቀጥታ፡

ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ክትትል የሚያደርግ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቋመ

አዲስ አበባ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) ኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ-19/ን ለመከላከል ክትትል የሚያደርግ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቁሟል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 80ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ክትትል የሚያደርግ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ማቋቋም ምክር ቤቱ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል ይገኝበታል።

በዚሁ መሰረት ስድስት አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲቋቋም የወሰነ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ኮሚቴውን ይመራል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የኮሚቴው አባላት ናቸው።

ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላው አጀንዳ የአርብቶ አደር ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ነው።

ፖሊሲው የአርብቶ አደሩን ለየት ያለ አኗኗር፣ የኑሮ መሰረትና ስነ-ምህዳር ከግንዛቤ በማስገባት በየዘርፉ ተበታትነው ሲተገበሩ የነበሩ የፖለሲና የስትራቴጂ ጉዳዮችን ወደ አንድ በማሰባሰብና በማቀናጀት፣ በተደጋጋፊነት ለመስራትና የተሻለ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀቱ ተመልክቷል።

የሠላም ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ አኳያ በመቃኘት ሁሉም የልማት ኃይሎች ለአርብቶ አደሩ ኑሮ የድርሻቸውን በተጠያቂነት መርህ መወጣት ይችሉ ዘንድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ያዘጋጀውን የአርብቶ አደር ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ለምክር ቤቱ አቅርቧል።   

ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ ፖሊሲው በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

ሌላው የምክር ቤቱ አጀንዳ ደግሞ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ረቂቅ ፖሊሲን የተመለከተው ጉዳይ ነው።

የቋንቋ መብት ሕገ መንግስታዊ እውቅና ቢያገኝም ራሱን የቻለ የቋንቋ ፖሊሲ ስላልዳበረ በቋንቋ አጠቃቀም፣ ልማትና ጥበቃ ረገድ የሚነሱ ችግሮች የሚፈቱበት የአሰራር ስርዓትና መርህ ማበጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።

የቋንቋ ፖሊሲው መታየት ያለበት ከመብትና ከእኩልነት አንጻር ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ከሚፈለገው አንድ የጋራ ማህበረሰብ ግንባታና ኢትዮጵያዊያን ከሚጋሩት ራዕይ ጋር ተቆራኝቶ መሆን እንዳለበትም ከግንዛቤ መግባቱ ተጠቅሷል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ያዘጋጀውን የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ረቂቅ ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ተወያይቶና ማስተካከያዎችን አክሎበት በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ እንዲውል በተፈራረመው የ65 ሚሊዮን 350 ሺህ ዶላር የብድር ስምምነት ላይም ተወያይቷል።  

ፕሮጀክቱ የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የኑሮ መሰረት እንዲሻሻል፣ እንዲጠናከርና እንዲያድግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ትግበራን መደገፍ ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

ለፕሮጀክቱ የሚሰጠው ብድር ምንም አይነት ወለድ የማይታሰብበት፣ በረጅም ዓመታት የሚከፈልና ከኢትዮጵያ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም እንደሆነ የገለጸው ምክር ቤቱ ስምምነቱን ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመራ ወስኗል።

ምክር ቤቱ በመጨረሻ የተወያየበት አጀንዳ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው።

ማንኛውም ጉዳይ የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወንና የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡን አስመልክቶ ብሔራዊ ጥቅምን የሚነካ ድርድር እንደማያደርግ ምክር ቤቱ አስታውቋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም