ቀጥታ፡

ፌዴሬሽኑ ከኤሲሚላንና ፍላሚንጎ የእግር ኳስ ክለቦች ጋር በመተባበር በታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ ሊሰራ ነው

አዲስ አበባ፣የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጣሊያኑ ኤሲሚላንና ከብራዚሉ ፍላሚንጎ ክለብ ጋር በመተባበር በታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮጀክት ላይ ሊሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መኮንን ኩሩ እንደገለፁት፤ የአገሪቱ እግር ኳስ በእድገት ላይ በመሆኑ አቅም ካላቸዉ ተቋማት ጋር በመተባበር መስራት ያስፈልጋል።

ለዚህም እንዲረዳ ከጣሊያኑ ኤሲሚላንና ከብራዚሉ ፍላሚንጎ ጋር በስፖርቱ ልማት ላይ በቅንጅት ለመስራት እንደተዘጋጁ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በየደረጃዉ የታዳጊዎችና የወጣቶች ማሰልጠኛ አካዳሚዎች ስለሚያስፈልጉት ከሁለቱ ክለቦች ጋር ማሰልጠኛ ማዕከላቱን ለመክፈት ድርድር ለማድረግ ማሰባቸውን አስታዉቀዋል።

በተጨማሪም ከጀርመን የእግር ኳስ ፌደሬሽንና ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም ከባየር ሙኒክ እግር ኳሰ ክለብ ጋር በመተባበር በእግር ኳስ እድገትና በታዳጊዎች ስልጠና ላይ እየሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል።

የባየር ሙኒክ የእግር ኳስ ክለብ ሙኒክ ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2012  በሚያከናውነው የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተጫዋቾች የተመረጡበት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም መካሄዱን ተናግረዋል።

ትናንት በተደረገ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ 16 ቡድኖች ተሳትፈዉ 10 ተጨዋቾች ለሙኒኩ ውድድር መመረጣቸዉን ገልፀዋል።

የባየር ሙኒክ  የእግር ኳስ ልዑክ ከየካቲት 16 እስከ የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ለሶስት ቀናት ለጀማሪ አሰልጣኞችና ለፕሪሚየር ሊጉ የሴቶችና ወንዶች የእግር ኳስ  ክለብ አሰልጣኞች በንድፈ ሀሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም