ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ ሰው የለም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ ሰው የለም
አዲስ አበባ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲያዎች የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ አድርገው የሚሰራጩት መረጃዎች ፈጽሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን በኮሮናቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) መያዙ የተረጋገጠ ሰው የለም።
በትናንትናው እለት አንድ ቻይናዊ በበሽታው እንደተያዘ ተደርጎ በማሕበራዊ ሚዲያ የተናፈሰው መረጃ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ገልጸዋል።
ግለሰቡ በለይቶ ማቆያ እንደነበረ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማምሻውን በተደረገለት ምርመራ ከበሽታው ነጻ እንደሆነ መረጋገጡን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን የቁጥጥርና የክትትል ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ መግለጹ ይታወሳል።
በአገር አቀፍ ደረጃም ኮቪድ-19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።
በተለይም ከቻይና እና ቫይረሱ ከተከሰተባቸው አገሮች የሚመጡ መንገደኞችን የሙቀት መጠናቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን በማጣራት አስቀድሞ ለመከላከል ከአየር መንገድ ሳይወጡ ምርመራ እየተደረገላቸው ነው።
ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰባቱ መግቢያዎች መንገደኞች በሙቀት ልየታ እንዲያልፉ እየተደረገ ይገኛል።
እስካሁንም በኮቪድ-19 ተጠርጥረው የነበሩ በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርጎ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉ ይታወቃል።