ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከሰመራና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሄዱ

ሰመራ ሰኔ 21/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአፋር ክልል ከሰመራና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ውይይት አካሄዱ። የሰመራና የአካባቢው ነዋሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ በክልሉ እየተካሄዱ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች በአፋጣኝ እንዲጠናቀቁ ጠይቀዋል። ድርቅ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ የተጀመሩ የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ስራዎች እንዲጠናቀቁም ጠይቀዋል። የፈንታሌና የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ፣ በመንደር የማሰባሰብ ስራዎች፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሰረተ ልማት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ ያልቻሉ በመሆናቸው የመንግስትን ትኩረት የሚሹ እንደሆነ አመልክተዋል። የአዋሽ፣ ወልዲያ ሀራ ገበያ መንገድ የባቡር መስመር ዝርጋታ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ከግምት ውስጥ ያስገባ አለመሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ ኢትዮጵያና ኤርትራን በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ የተቀበረው ፈንጂ እንዲመክን፣ የትጥቅ ትግልን መርጠው ትግል እያካሄዱ የሚገኙ ኃይሎች ጥሪ እንዲደረግላቸውና ሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል። የጨው አምራቾች አዮዳይዝድ የሆነ ጨው የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ እንዳያመርቱ ገደብ የተደረገባቸው በመሆኑ ገደቡ ተነስቶላቸው አቅማቸው የሚችለውን ያህል እንዲያመርቱ ፈቃድ ጠይቀዋል። የክልሉ ህዝብ በፌዴራል መንግስት ውስጥ ያለው የስልጣን ውክልና በቂ እንዳልሆነ በመግለጽ ጥያቄዎችን አንስተዋል። አፋርን ጨምሮ በአማራ፣ ኦሮሚያና ሸረሪ ክልሎች የሚገኙ የአርጎባ ህዝቦች ህገ መንግስታዊ መብታችን ይከበር በሚል ጥያቄም አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዋሪዎቹ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ወደ አፋር ክልል በመሄድ ከህዝቡ ጋር መተዋወቅና መወያየት ያልቻሉት በመሃከል ላይ የረመዳን ጾም ስለነበረ ነው። በክልሉ ያለው የመሰረተ ልማት መዘግየት እንዳለ ሆኖ የሰመራ አየር ማረፊያን ጨምሮ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን ማድነቅ ተገቢነት እንዳለው አስገንዝበዋል። ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በሚመለከት መዘግየት የታየው በክልሉ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ በሚገኙ ፕሮጀክቶች እንደሆነ መገምገሙን ዶክተር አብይ ጠቅሰው በሚቀጥለው አመት ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ''በምንናገረው ልክ መተግበር አለመቻላችን ክፍተት ፈጥሯል'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመፈጸም አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል። የፕሮጀክቶቹን ችግር በመለየት መፍትሄ ለመስጠት ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። ከኤርትራ ጋር የሚደረሰው ስምምነት ከማንም በላይ የአፋርን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር አብይ አካባቢውን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ከሁለቱም ወገን እንዲሰራ የሚያስችል የሰላም ሂደት መጀመሩን አስገንዝበዋል። የትጥቅ ትግልን መርጠው ሲታገሉ የነበሩ አካላት የሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ''ከትጥቅ ትግል ወደ ጭንቅላት ትግል መሸጋገር ያስፈልጋል'' ብለዋል። አርጎባን በሚመለከት የቀረበው ጥያቄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን በህገ መንግስቱ መሰረት ምላሽ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። በአጠቃላይ የክልሉን የልማት ጥያቄ ለመመለስ መንግስት እንደሚሰራ ተናግረው ዛሬ የተጣለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ የዚህ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም