በመላው አገሪቱ ተከስቶ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ችግር ተፈቷል - ኢዜአ አማርኛ
በመላው አገሪቱ ተከስቶ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ችግር ተፈቷል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) ከትናንት ምሽት ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር መፈታቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ትናንት በመላው አገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ችግር ከግልገል ጊቤ 2 የሀይል ማመንጫ መስመር ጋር የተያያዘ ነው።
''ችግሩ ንፋስ በቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያ የተከሰተ ሲሆን ከጊቤ ሁለት የሀይል ማመንጫ የሚነሳው 400 ኪሎ ቮልት ሀይል ተሸካሚ ከፍተኛ መስመር ተቋርጦ ነበር'' ብለዋል።
ችግሩ የተከሰተው ማምሻውን በመሆኑና ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ሀይል ጥቅም ላይ የሚያውልበት ሰአት በመሆኑ ከቀሩት የሃይል ማመንጫዎች ፍላጎቱን ማሟላት ሳይቻል መቅረቱን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት ከጊቤ 3 የሚነሳው እና የበርካታ የአገሪቱ ክፍሎችን የሀይል ፍላጎት የሚያሟላው መስመርም በደረሰበት ጫና ሳቢያ የኤሌክትሪክ ሃይል ሙሉ ለሙሉ ሊቋረጥ እንደቻለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የችግሩ መንስኤ በመታወቁ አብዛኛዎቹ ኃይል ተቋርጦባቸው የነበሩት አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል።
ነገር ግን አሁንም በአንዳንድ መስመሮች ላይ ደህንነታቸውን የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ በመሆኑ በተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም የሀይል መቋረጥ እንደሚታይ አመልክተዋል።