የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሰብዓዊነት ባለፈ ለአገር እድገት መዋል እንዳለበት ተጠቆመ

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከሰብዓዊ እርዳታ ባለፈ ለአገር የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት ሊውል እንደሚገባ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬት ከአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጋር በመተባበር “በጎነት ለአብሮነት” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት "የሰርዶ በጎ ፈቃድ አገልግሎት" መስራችና ሊቀመንበር አቶ አክሊሉ ስመኝ የበጎ ፈቃድ መርህ ዘላቂነት ባለው መልኩ በማህበራዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ በትኩረት መስራት መሆኑን ነው የገለጹት።

አገልግሎቱ በተለይ አብሮነትን በማጠናከር ለአንድነትና ለሰላም ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ለማሳካት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ አካላት መርሆቹን ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከሰብዓዊ እርዳታ ባለፈ ለአገር የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት እንዲውል ማድረግ እነደሚገባም ጠቅሰዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት በአዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ አካባቢ የተቋቋመው  "የፍቅር ለነዳያን በጎ አድራጎት ማህበር" አባላት ወጣት ስንታየሁ ጌታየሁ እና ወጣት ቶሎሳ ታከለ እንደገለጹት በጎ ፈቃደኝነት በራስ ተነሳሽነት የሚሰራና የውስጥ ፍላጎትን የሚጠይቅ ነው፡፡

በአካባቢያቸው በራስ ተነሳሽነት ባቋቋሙት ማህበር ዘወትር እሁድ የነዳያንን ሰውነት በማጠብ፣ የግል ንፅህናቸውን በመጠበቅና ልጆቻቸውን በመንከባከብ እያገለገሉ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡

በመልካም ተግባር ላይ መሰማራታቸው  ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች  እገዛ ገመስጠት  ባለፈ  እያከናወኑት ያለው ተግባር በሌሎች እውቅና እየተሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በፋና ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬት የትብብር ፕሮግራም ክፍል ዳይሬክተር  አቶ አዳም  ታደሰ እንደገለጹት አብሮነትን ለማጠናከርና በጎ ፈቃደንነትን ለማስቀጠል ድጋፍ ማድረግ ይገባል።

የመድረኩ ዓላማም በራስ ተነሳሽነት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰማሩ  ማህበራትን  ለማበረታታትና ለማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ አላስፈላጊ ድርጊቶችና መገፋፋቶችም የኢትዮጵያዊያን መገለጫዎች አለመሆናቸውን አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት  ኤጀንሲ ምክትል  ሥራ አስኪያጅ  ወይዘሮ ነጻነት ዳባ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስካሁን በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም አብሮነትን በማጠናከር በኩል የተሰሩ ሥራዎች እምብዛም ናቸው ይላሉ።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራትና  በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ  ተቋማት ተሳትፈው ተሞክሮዎቻቸው ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም