በአምቦ ከተማ ህገወጥ ንግድን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በአምቦ ከተማ ህገወጥ ንግድን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ
አምቦ ሰኔ21/2010 በአምቦ ከተማ ህገወጥ ንግድን በመከላከል የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን የከተማዋ ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ገለጸ። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መርጋ ወዳጆ ለኢዜአ እንደገለጹት ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በጥናት ከመለየት ባለፈ ጽህፈት ቤቱ የመፍትሄ እርምጃ እየወሰደ ነው። በጥናቱ በከተማዋ በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ከተለዩት 2 ሺህ 102 ነጋዴዎች ውስጥ 1 ሺህ 46 የሚሆኑት ከተፈቀደላቸው ንግድ ፈቃድ ውጭ ሲሰሩ የተገኙ መሆናቸውንም አመልክተዋል። ከተፈቀደላቸው ምርት ውጭ ሌላ ምርት ቀላቅለው የሚሸጡ ነጋዴዎች የተፈቀደላቸውን ምርት ብቻ እንዲሸጡ እንዲሁም ፍቃድ ካወጡበት ዘርፍ ውጪ በተለያየ ንገድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችም የንግድ ሥራ ማስፋፊያ ፍቃድ እንዲሰጣቸው መደረጉን አቶ መርጋ ገልጸዋል። በተጨማሪም ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት፣ ንግድ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች ወደህጋዊ የንገድ እንቅስቃሴ እንዲገቡ የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። ህገወጦችን ወደ ህጋዊ የንግድ አሰራር ለመምጣት የሚደረገውን ጥረት ተቀብለው ፈቃደኛ ባልሆኑ 398 ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም አመልክተዋል። አቶ መርጋ እንዳሉትበተለያዩየተሀድሶመድረኮችከንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ጀምሮ የመልካም አስተዳደር መጓደልና ኪራይ ሰብሳቢነት መሰራፋት ለህገወጥ ንግድ መስፋፋት በር መክፈቱን ሕዝቡ አንስቷል፡፡ እርምጃውም የእዚህ አካል መሆኑን ጠቁመው፣ በንግድ ስርዓቱ እንቅስቃሴ ላይ የሚታዩ ማናቸውም ህገ ወጥ ተግባራት የንግድ እነቅስቃሴውን የሚጎዱ በመሆኑ የከተማው ህዝብ በማጋለጥ ሊታገላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የአምቦ ከተማ ወጣት አቤል መንግስቱ በሰጠው አስተያየት እሱና መሰሎቹ ቤት ተከራይተውና ንግድ ፈቃድ አውጥተው በህጋዊ መንገድ መስራት ሲችሉ የጎዳና ንግድ መምረጣቸውን ተናግሯል፡፡ "ንግድ ፍቃድ አውጥተን ህጋዊ ለመሆን ብንፈልግም ለግብርና ለቤት ኪራይ የሚጠየቀው ዋጋ ከአቅም በላይ በመሆኑ አግባብ ባይሆንም የጎዳና ንግድ ሥራችንን ቀጥለናል" ብሏል። በከተማው አጠቃላይ ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማራችው ወጣት የኔነሽ ንጉሴ በበኩሏ በሰጠችው አስተያየት "የህገ-ወጥ ንግድ መስፋፋት ግብር ከፋዩን ነጋዴ ከገበያ እንዲወጣ እያስገደደው ነው " ብላለች። ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ትክክለኛነቱና የጥራት ደረጃው ያልተረጋገጠ ምርት ለገበያ በማቅረብ በሸማቹም ሆነ በህጋዊ ነጋዴው ላይ ችግር አየፈጠሩ መሆኑን ገልጻለች፡፡ የኔነሽ እንደምትለው ህገ-ወጦችን ወደ ህጋዊነት ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው። በተሽከርካሪ ጋሪ አልባሳትን በማዘዋወር በጎዳና ላይ ንግድ መሰማራቱ የገለጸው ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት አብደላ መሀመድ ነው። በህጋዊ መንገድ መንቀሳቀሰ ያለውን ፋይዳ እየተገነዘበ በመምጣቱ በቀጣይ የንግድ ፍቃድ አውጥቶ በህጋዊነት ለመንቀሳቀስ ማቀዱን ተናግሯል።