ቀጥታ፡

2ኛው አገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ሰኔ 22 እና 23 በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 ሁለተኛው አገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ መንግስት እያከናወነ ያለውን የለውጥና የተሃድሶ ሂደት የማዳበር ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መለስ ዜናዊ አካዳሚ 2ኛውን አገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መገለጫ ሰጥቷል። የአካዳሚው ጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደምሴ ሽቶ እንደተናገሩት፤ የተለያዩ ምሁራን በሚሳተፉበት  ኮንፍረንስ ላይ የሚቀርቡት  የምርምር ጽሁፎች "መንግስት አሁን እያደረገ ያለውን የተሃድሶና የለውጥ ሄደት ከማገዝ አኳያ ከፍተኛ ሚና አላቸው"። ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይህ ኮንፍረንስ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገውም በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አስተሳሰብ፣ በልማታዊ ኮምዩኒኬሽንና ሚዲያ ስራዎች እንዲሁም በፌደራሊዝምና አጠቃላይ መንግስት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ  መሆኑ ተገልጿል። የጥናትና ምርምር ውጤቶች  ቀርበው ግብዓት የሚገኝበት ጠቃሚ ውይይት እንደሚሆንም ተጠቁሟል። በኮንፍረንሱ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና ምሁራን እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት እንደሚሳተፉ ተገልጿል። በአጠቃላይ የተሳታፊዎች ቁጥር ከሶስት መቶ በላይ ሲሆን ኮንፍረንሱም ከሰኔ 22 እስከ 23 በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም