የልማት ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን ወደ 34 በመቶ ዝቅ ብሏል

123

የካቲት 19/2012  (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ የብድር መጠኑ ከነበረበት 40 በመቶ ወደ 34 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገለጸ። 

ከተበላሸ ብድር ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለሱንም ገልጿል።

ባንኩ የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለእየሱስ በቀለ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ባንኩ የሚሰጣቸው ብድሮች በወቅቱ ባለመመለሳቸው የተበላሸ ብርድ መጠኑ ሲጨምር ቆይቷል።

ከብድር መፍቀድና አስተዳደር ጋር በተገናኘ የፖሊሲ ክፍተት በመኖሩ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአገሪቷ የነበረው የሠላም እጦት በፕሮጀክቶች ውጤታማነት ላይ ጫና ማሳደሩና የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ለተበላሸ ብድር መጠኑ ምክንያቶች መሆናቸውን ጨምረዋል።

ተጠያቂነት ከማስፈን አንጻር ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየተወሰደና ችግሩ በተገኘባቸው ፕሮጀክቶች ላይም ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል።

የመክፈል አቅማቸው አጠራጣሪ ለሆኑ ፕሮጀክቶች ብድር አለመስጠት በመፍትሄነት ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል በፕሬዚዳንቱ መግለጫ ተጠቅሷል።

በዚህም የተበላሸ የብድር መጠኑን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 40 በመቶ ወደ 34 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ለብድር መበላሸት ትልቁ ችግር በዝናብ የሚለሙ እርሻዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ኃይለእየሱስ ጥለው የጠፉ አልሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በስድስት ወራት ውስጥ ከተበላሸ ብድር ከ202 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስ የተቻለ ሲሆን 57 ፕሮጀክቶች ደግሞ አገግመው ወደ ስራ እንዲመለሱ ተደርጓል።

በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የባንኩን የተበላሸ የብድር መጠን ወደ 10 በመቶ ለማውረድ ዕቅድ እንደተያዘም ተገልጿል።

የልማት ባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን ተቀባይነት የሚኖረው 15 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከገባበት ኪሳራ ወጥቶ በግማሽ ዓመቱ ከ951 ሚሊዮን ብር በላይ ከታክስ በፊት ትርፍ ማግኘቱም ተገልጿል።

የባንኩ አጠቃላይ የሃብት መጠን ከ89 ቢሊዮን ብር በላይ፤ የብድር ክምችቱ ደግሞ 47 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም