ለወጣቶች የሰላም አምባሳደርነት ዕውቅና ተሰጠ

116

ዲላ  የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሰማርተው ውጤት ላመጡ 250 ወጣቶች የሰላም አምባሳደርነት እውቅና ተሰጠ።

ለወጣቶቹ የሰላም አምባሳደርነት እውቅና የተሰጣቸው በሁለቱ ዞኖች 13 ወረዳዎች ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ባከናወኑት  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው።

በቡሌ ሆራ ከተማ ተገኝተው ለወጣቶቹ  እውቅና የሰጡት የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ  እንዳሉት በጌዴኦና ጉጂ መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት አስከፊ ጉዳት አስከትሎ አልፏል።

በአካባቢው የነበረው ችግር ተፈቶ በአጭር ጊዜ ውሰጥ በህዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲዳብር በበጎ ፍቃድ የተሰማሩት  ወጣቶች ያከናወኑት ስራ ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።

አካባቢው እንዳይረጋጋ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመከላከልና ጥፋተኞችን አሳልፎ በመስጠት ወጣቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

ያለፈው ክፉ ቀን ዳግም እንዳይመጣ የሰላም አምባሳደር የሆኑ ወጣቶችም ሌሎችንም በማስተማር አካባቢው የሰላምና የልማት ቀጠና እንዲሆን የመስራት ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት ወጣቶችን ከየወረዳው መልምሎ በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ዙሪያ ስልጠና በመስጠት ለአከባቢው ሰላምና መረጋጋት ላበረከተው አስተዋጾም ምስጋና አቅርበዋል።

ከምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ የመጣው ወጣት ሙሉቀን አብርሃም በሰጠው አስተያየት "ወረዳው በግጭቱ ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ስራ ስንገባ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሞን ነበር "ብሏል።

ሆኖም ለሰላም ሲባል ዋጋ እንከፍላለን በሚል ተዘጋጅተው ወጣቶች በሚገኙበት በተለይም ትምህርት ቤቶች ፣ የእምነት ተቋማትና መዝናኛዎች ስለ ሰላም በመስበክ ብዙዎችን መለወጥ እንደቻሉ ተናግሯል።

በአካባቢው የመጣውን የሰላም ውጤት በልማትም ላይ ለመድገም የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል።

ወጣቱ  በልማት ላይ  በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት እንደሚገባ የተናገረው ደግሞ ከጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ የመጣው ወጣት ደሳለኝ ሽፈራው ነው።

አክራሪነትን በመከላከልም ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም የጀመሩትን ስራ ለማጠናከር  የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።

በካቶሊክ እርዳታ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጆን ሽማይት በሁለቱ ዞኖች ከሚገኙ 13 ወረዳዎች የ250 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በመመልመል በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

ወጣቶቹም ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በየቀበሌያቸው ባከናወኑት ስራ ውጤት መገኘቱን ተከትሎ የሰላም አምባሳደር እውቅና እንደተሰጣቸው  አመልክተው ሰላም ለማረጋገጥ የተጫወቱት ሚና  የሚበረታታ  መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም