የኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለኬሚካል ኢንዱስትሪ ዕድገት ማነቆ ሆኗል

24

አዲስ አበባ የካቲት 19/2012 ( ኢዜአ) የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በዘርፉ ዕድገት ላይ ችግር ፈጥሯል አለ።

ኢንስቲትዩቱ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ዕቅድ አፈጻጸሙ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለኬሚካል ኢንዱስትሪ ዕድገት ተግዳሮት ሆነው ቀጥለዋል።

ከኃይል አቅርቦት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ እየተሰራ ቢሆንም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማቃለል እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት።

የኤሌክትሪክ አቅርቦት በፈረቃ በመሰጠቱ ሳቢያ በተለይም በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ በተከሰተው የምርት መቀነስ የዋጋ ጭማሪ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ከተጠቀሱት ችግሮች በተጓዳኝ የመሰረተ ልማት፣ የገበያ ትስስር ችግር በዘርፉ ለተሰማሩ ተቋማት ፈተና ሆነዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በግማሽ ዓመቱ የአቅም ግንባታ፣ የካይዘንና የተለያዩ ስልጠናዎችን ለተለያዩ ድርጅቶች መስጠቱንም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የግብዓት እጥረት፣ የገበያ ትስስር፣ የተቋማት በቅንጅት አለመስራት ችግሮች በሚፈልጉት መጠን ለመስራት እንዳላስቻሏቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም