በትግራይ ያለውን የማአድን ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው

ሽሬ እንዳስላሴ፣ የካቲት 19/2012 (ኢዜአ)  በትግራይ ክልል ያለውን እምቅ የማዕድን ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጁ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በማዕድን ሃብት የተሰማሩ ባለሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ትላንት  በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋአለም ሓድጉ እንደገለፁት ሀብቱ በአግባቡ ጥቅም እንዲሰጥ ከክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ፣  ከመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኙ የአስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

ይህም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች የተፈጥሮ ደንን ሳይጨፈጨፉና የአርሶ አደሮች የእርሻ መሬትን ሳይነኩ የማዕድን ሃብቱን ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል።

 "ባለሃብቶች ፈጥነው ወደ ማልማት ስራ እንዲገቡ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው" ብለዋል።

እንዲሁም ተጠንቶና ተለክቶ የተሰጣቸውን የማዕድን መሬት በገቡት ውል መሰረት እንዲያለሙና የስራ እድል እንዲፈጥሩም የአንድ ማዕከል አገልግሎት መመቻቸቱን አስረድተዋል።

ቀልጣፋ የስራ ፈቃድ አገልግሎት በዚሁ ማዕከል ያገኛሉ።

በኤጀንሲው የፈቃድ አሰጣጥና የማዕድን አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ፍሳሃ መረሳ በበኩላቸው በማዕድን ዘርፍ  ለመሰማራት የስራ ፈቃድ ከወሰዱት 26 ባለሃብቶች መካከል ሰባቱ ብቻ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

"ችግሩን የተከሰተው በባለ ሃብቶች የማስፈፀም አቅም ውስንነት ምክንያት ነው" ብለዋል።

የቀሩት ባለሃብቶች በሦስት ወራት ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ የመጨረሻ መስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ጠቁመዋል።

በመድረኩ ከተሳተፉት ባለሀብቶ መካከል አቶ አሰፋ ተገኝ እንዳሉት የግራናይት ማዕድን ለማልማት ከሁለት ዓመት በፊት ፈቃድ አግኝተዋል።

ወደ ማምረት ለመሸጋገር  የነበረባቸው የመንገድ ችግር  አሁን በመፈታቱ ወፍጥነት ወደ ማምረት ስራ ለመግባት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ምርቱን በሚያመርቱበት አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ  በሙሉ አቅም ማምረት ችግር እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ደግሞ ከ360 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በእምነ በረድ ማዕድን ልማት የተሰማራው የሳባ  እምነ በረድ ፋብሪካ ተወካይ አቶ አርአያ ገብረመድህን ናቸው።

በመድረኩ የተሳተፉት የሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ግደይ በየነ በሰጡት ምላሽም  የኃይል አቅርቦት ችግር እንደሌለ ገልጸዋል።

"ፋብሪካው ትራንስፎርመር መትከል ከቻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ይችላል "ብለዋል።

በትግራይ ክልል በጥናት ከተለዩት የማዕድናት ክምችት መካከል ደለል ወርቅ፣ ግራናይት፣ ጂብሰም፣ ብረትና እምነ በረድ እንደሚገኙበት በመድረኩ ተገልጿል።

በኢንዳስትሪያል ማዕድን ልማትና በጠጠር ምርት ለ925 ባለሃብቶችና ተቋማት የስራ ፈቃድ መስጠቱን ከክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም