በሀዋሳ ከተማ ዘመናዊ የቡና ምርት ግብይት ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ከተማ ዘመናዊ የቡና ምርት ግብይት ሊጀመር ነው
ሀዋሳ ሰኔ 21/2010 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ዘመናዊ የቡና ምርት ግብይት ሊጀምር መሆኑ ተገለጸ፡፡ በምርት ገበያው የሀዋሳ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ካሳዬ ማሴቦ እንደገለጹት በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የቡና ግብይት ስርዓት ለመጀመር ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ስርዓቱ በኮምፒውተርና በኢንተርኔት ኔትዎርክ ታግዞ ሻጭና ገዥ ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ ግብይት እንዲፈጽሙ ያስችላል ተብሏል፡፡ ቀደም ሲል አዲስ አበባን ብቻ ማዕከል አድርጎ ድምጽን በማስተጋባት ግብይቱ ይፈጸም ነበር ያሉት አቶ ካሳዬ፤ የአሁኑ ቴክኖሎጂ ግን ቡና አምራች ገበሬዎች ከሀዋሳ ቀጥታ አዲስ አበባ ካሉ ነጋዴዎች ጋር የሚገበያዩበት ስርዓት ነው ብለዋል፡፡ ይህም ቀደም ሲል ቡና አምራች ገበሬዎች ለደላሎች የሚከፍሉትን ክፍያ አስቀርቶ ተጠቃሚነታቸውን ያሳድጋል ሲሉም አቶ ካሳዬ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግም አንዳንድ የቴክኒክ ስራዎችና የፍቃድ ጉዳይ ብቻ እንደቀረም ተጠቅሷል፡፡ ቴክኖሎጂው በተያዘው አመት በሀዋሳ ወደ ስራ ይገባል ያሉት አቶ ካሳዬ፣ ለቡና ሻጮቹ ገበሬዎችም ስለግብይት ስርዓቱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስልጠናም እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ የሚተገበረው ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ቡና አምራች ገበሬው ዘመናዊ የግብይት እውቀትና ክህሎት እንዲኖረው ያስችላል፡፡ በተጨማሪም የዘመናዊ የግብይት ስርዓቱ የምርት ደረጃና ጥራትን በማስጠበቅና ግልጽ አሰራር በማስፈን በኩልም የላቀ ጠቀሜታ እንዳለውም ተጠቁሟል፡ በቀጣይም በነቀምቴ፣ ሁመራ እና ጅማ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የምርት ማገበያየት ስርዓት ለመዘርጋት የመሰረት ልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አቶ ነጻነት ገልጸዋል፡፡