ቀጥታ፡

የደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥያቄ በጥናት ላይ የተመሰረተ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠዋል- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ

የካቲት 18/2012 የደቡብ ክልልን የአደረጃጀት ጥያቄ ለመመለስ በቅርቡ የተቋቋመው ኮሚቴ በሚያቀርበው ጥናት መሰረት መንግስት አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

በዱራሜ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ለተመሳሳይ ውይይት ሀላባ ቁሊቶ ገብተዋል::


በደቡብ ክልል ከንባታ ጠንባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዱራሜ ስታዲየም ለተሰበሰቡት በሺዎች ለሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል።

ከንግግሩ በኋላ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የመሰረተ ልማትና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ከመንግስት ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በተለይም የመንገድ፣ የውሃና የመብራት መሰረተ ልማት እንዲሟላ እንዲሁም ከልዩ ወረዳ እና ከክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ የሚያነሳው ጥያቄ እንዲመለስ ተጠይቋል።

ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ የአካባቢውን የውሃና የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው አካባቢውን በመንገድ መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የሚያስችል ዕቅድ በመንግስት እንደተያዘ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው በዞኑ እየተነሳ ያለውን የልዩ ወረዳ አደረጃጀት ጥያቄ ክልሉ ጥናት አድርጎ ምላሽ የሚሰጥበት እንደሆነ አመልክተዋል።

ክልል ከመሆን ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ በደቡብ ክልል ለሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የክልሉ ተወላጆች አባል የሆኑበት ኮሚቴ በቅርቡ መቋቋሙን አስታውሰዋል።

ይህ ኮሚቴ ጥናት አድርጎ በሚያቀርበው ውጤት መሰረት መንግስት አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም