ለቶኪዮ ኦሊምፒክ በሴቶች የብስክሌት ተወዳዳሪ ለመምረጥ ውድድር ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ፣የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) በቶኪዮ ኦሊምፒክ በሴቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ የብስክሌት ተወዳዳሪ ለመምረጥ በመቐሌ ከተማ የማጣሪያ ውድድር ሊካሄድ ነው።

ዓለም አቀፍ የብስክሌት ኅብረት (UCI) ኢትዮጵያ ዘንድሮ በቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው ኦሊምፒክ በሴቶች ብስክሌት በአንድ ተወዳዳሪ እንድታሳትፍ መወሰኑ ይታወቃል።

ኅብረቱ ይህን የወሰነው ባለፉት ሁለት ዓመታት በአፍሪካ በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያ በሴት ብስክሌት ተወዳዳሪዎች ያስመዘገበችውን ውጤት መሠረት በማድረግ ነው።

በመሆኑም በቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን የምትወክል ብስክሌተኛ ለመምረጥ ከየካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በመቐለ ውድድር ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ ከትራንስ ኢትዮጵያ፣መሰቦ ሲሚንቶ፣መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግና መቐሌ ከተማ ክለቦች የተወጣጡ 25 አዋቂ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ቢስክሌት ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ግዛቸው መኮንን ገልጸዋል። ።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት በአገር ውስጥና በውጭ በተካሄዱ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያላቸው ሲሆኑ  240 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ውድድር ያደርጋሉ።

በሶስት ዙሮች በሚካሄዱት ውድድሮች በድምር ውጤት የተሻለ ነጥብ ያላት አንድ ብስክሌተኛም ተመርጣ ቶኪዮ ላይ ኢትዮጵያን ትወክላለች።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በባህር ዳር፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄዱት የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮናዎች በሴቶች በተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ በብስክሌት በአንድ ተወዳዳሪ እንድትወከል እድል ተሰጥቷታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም