በአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ እየተሻሻለ ነው

100

አዲስ አበባ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ እየተሻሻለ መምጣቱን ታራሚዎች ገለጹ። የፌዴራል ማረሚያ ቤት በበኩሉ በታራሚዎች አያያዝ "የሥነ ምግባር ግድፈት በታየባቸው ፖሊሶች" ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል። 

ይህ የተገለጸው የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ በባህርዳር ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው።

ጉባኤው ለሦስት ቀናት የተካሄደ ሲሆን ኮሚሽነሮቹ በሚመሯቸው ማረሚያ ቤቶች በተገበሯቸው ማሻሻያዎች ዙሪያ ልምድ ተለዋውጠዋል።  

ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ  የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት የተጎበኘ ሲሆን፤ የክልልና ፌዴራል ማረሚያ ቤት ሃላፊዎች በስፍራው በመገኘት ተሞክሮ ቀስመዋል።

በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ታራሚዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በማረሚያ ቤቱ ሰብአዊ መብታቸው ተጠብቆ በአግባቡ እየታነጹ ነው።

''አሁን ባለው ሁኔታ ከማረሚያ ቤት ፖሊሶች ጋር ያለን ግንኙነት ጥሩ ነው'' ያሉት ታራሚዎቹ፤ ''በማረሚያ ቤት ውስጥ የተለያዩ አዝዕርቶችን በማምረት ራሳችንን እየደጎምን ነው'' ብለዋል።

የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወንድም አገኝ ወዳጅ  በበኩላቸው ቀደም ሲል የነበረው የታራሚ አያያዝ ሰብዓዊ መብትን የሚነካና ብዙ ጉዳቶችን ያስከተለ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንንም ሁኔታ ለመቀየር ከላይ ካለው መዋቅር ጀምሮ ታራሚዎችን ማወያየት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በዚህም የሰብአዊ መብት አያያዙ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ኮሚሽነር ጄነራል ጀማል አባሶ እንደሚናገሩት፤ በማረሚያ ቤቶች የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ።

በተለይ ለፖሊስና አስፈጻሚዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጡ አጫጭርና ረዥም ስልጠናዎች መሰጠቱን ነው የተናገሩት።

በታራሚዎች በኩል የተፈጠረውን አንጻራዊ ነጻነት በአግባቡ ያለመጠቀም ችግሮች መስተዋላቸውን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ ይሄንንም ለማስተካከል የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አክለዋል።

''አሁን ባለው ሁኔታ በብዙዎቹ ማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት ጥሰት ቆሟል'' ነው ያሉት።

እንደ ኮሚሽነር ጀነራል ጀማል ገለጻ፤ የስነ ምግባር ግድፈት የታየባቸው ከ100 በላይ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም