በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የነበሩ 63 ሰዎች ክሳቸው መቋረጡን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ

68

አዲስ አበባ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የነበሩ 63 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን አስታወቀ።

ክሱ የተቋረጠው ለአገራዊ አንድነትና ለለውጡ የሚኖረው ፋይዳ ከግምት ውስጥ ገብቶ እንደሆነ ተገልጿል።

ክስ ማቋረጥ ማለት ክሱ ሙሉ በሙሉ ይቆማል ማለት እንዳልሆነም ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ እና የመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ እንደተነገረው፤ የክስ መቋረጥ ሂደቱ የተከናወነው የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋል ተብሎ በመታመኑ ነው።

ዐቃቤ ህግ ክስ ተቋርጦላቸው እንደገና በወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችን ክስ መልሶ ማንቀሳቀስ ይችላልም ሲሉ ተናግረዋል።

ክስ ተመስርቶባቸው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ክስ ማቋረጥ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፋ ከሆነ ክሱ እንዲቋረጥ ይደረጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መናገራቸው ይታወሳል።

ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉ ግለሰቦች መካከልም በሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በተለይም በሜቴክ ውስጥ ከተፈፀመ ሙስና እና ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ  የአመራርነት ሚና ያልነበራቸው ግለሰቦች ክሳቸው መቋረጡ ተነስቷል።

በተጨማሪም ከሰኔ 15 ሁከት እና በሲዳማ ዞን ተከስቶ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግለሰቦች ክሳቸው ከተቋረጠላቸው መካከል ይገኙበታል ተብሏል።

በአራት የወንጀል ድርጊት ማለትም በግድያ፣ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ዘረፋዎች፣ አስገድዶ መድፈር እና በወንጀል ማነሳሳት ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ክስ እንደማይቋረጥ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም