'ውበትን ፍለጋ' ተውኔት ከ16 ዓመታት በኋላ ለህትመት በቃ - ኢዜአ አማርኛ
'ውበትን ፍለጋ' ተውኔት ከ16 ዓመታት በኋላ ለህትመት በቃ
አዲስ አበባ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) በአንጋፋው ሁለገብ የጥበብ ሰው ጌትነት እንየው የተደረሰው 'ውበትን ፍለጋ' የተሰኘው ተውኔት ከ16 ዓመታት በኋላ ለህትመት በቃ።
መፅሐፉ በርካታ የጥበብ ቤተሰቦች በተገኙበት ደማቅ የጥበብ ድግስ ተደግሶ ትናንት ማምሻውን ተመርቋል።
"ውበትን ፍለጋ" የተሰኘው የአርቲስቱ ባለአራት ገቢር ተውኔት ከ1992 እስስ 1996 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ዓመታት በብሔራዊ ቴአትር ለተመልካች የቀረበና በዘመኑ ለረጅም ጊዜ መድረክ ላይ የቆዬ ብቸኛ ተውኔት ነበር።
ተውኔቱን ጸሀፈ ተውኔቱ ራሱ አዘጋጅነት፣ ተስፋዬ ገብረሃብና በረዳት አዘጋጅነት እንዲሁም ሉሌ አሻጋሪ በዝግጅት አስተባባሪነት ለመድረክ የበቃ ሲሆን ከያኒያን መካከል ደግሞ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ሙሉዓለም ታደሰ፣ ተዘራ ውብሸት፣ ተክሌ ደስታ፣ ሀረገወይን አሰፋ ይገኙበታል።
በርካታ ተውኔቶች በአጭር ጊዜ ከመድረክ በሚወርዱበት ዘመን በመድረክ ላይ መታየቱ ተወዳጅ እንደነበርና የህሊና እርካታ ይሰጠው እንደነበር ፀሐፈ ተውኔቱ ገልጿል።
ተውኔቱ እንዲታተም ከ12 ዓመታት በፊት በወዳጆቹ ግፊት ተደርጎበት ለሕትመት ቢያዘጋጀውም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለሕትመት አለማብቃቱን አርቲስት ጌትነት አስታውሷል።
ተውኔቱ በመፅሐፍ መውጣቱ በዘመኑ የነበረውን ትውልድ አስተሳሰብ ለመረዳት እንደሚያግዝ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ስለተውኔት የአፃፃፍ ብልሀት /ቴክኒክ/ የቴአትር ጥበብ ተማሪዎች ተጨማሪ የማስተማሪያ ሀብት ጠቀሜታ እንደሚኖረው አብራርቷል።
የተውኔቱ መቼት ቦታውን አዲስ ከበባ፣ ዘመኑንም 1960ዎቹ ላይ ያደረገ ነው።
ተውኔቱ ከዚህ በፊት በፊልም መልክም ተሰርቷል።
በ139 ገፆች የተቀነበበው 'ውበትን ፍለጋ' ተውኔት በ90 ብር ለገበያ ቀርቧል።
አርቲስት ጌትነት እንየው ከ17 በላይ ተውኔቶችን በመፃፍ፣ ከ23 በላይ ተውኔቶችን በማዘጋጀት፣ ከ27 በላይ ተውኔቶች ላይ ደግሞ በመሳተፍ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ደማቅ አሻራው ያሳረፈ አንጋፋ የጥበብ ሰው ነው።
ከተውኔቱ በተጨማሪም በተለያዩ የሬዲዮና በቴለቪዥን ድራማዎች በፀሀፊነትና ተዋናይነት የተሳተፈ ሲሆን 'እውቀትን ፍለጋ' የተሰኘ የግጥም መድብልም አሳትሟል።
ከዚህ በፊት 'እቴጌ ጣይቱ' የተሰኘ ተውኔት ያሳተመው ፀሐፈ ተውኔቱ በቀጣይም ሌሎች ተውኔቶችን አሰባስቦ በጋራ ለማሳተም ሀሳብ እንዳለው ገልጿል።
አንድ ምዕተ ዓመት ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ተውኔት ታሪክ 261 በሚሆኑ ተውኔቶች ለመድረክ ቢበቁም ለሕትመት የበቁት እጅግ አናሳ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ ገልጸዋል።
ተውኔቶች ለሕትመት ብርሐን ባለመብቃታቸው በኢትዮጵያ ተውኔት ታሪክ ላይ ምርምር ለማድረግ አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸው፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ ቴአትሮች እንዲታተሙ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል።
በምረቃ ስርዓቱ ላይ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰዎች ስለ አርቲስቱ ሙያዊ ተሰጦ፣ አገር ወዳድነቱ፣ መልካም ስብዕና በማድነቅ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
አርቲስቱ ከ35 ዓመት በላይ የብሔራዊ የቴአትር ቆይታው በርካቶችን ያስተማረ፣ ስራዎቹም በታሪክ፣ ባህልና አገራዊ አንድነት ላይ ያተኮሩና ተወዳጅነትን ያተረፉ እንደነበረ ተናግረዋል።
አርቲስቱ በኪነ ጥበብ አበርክቶቹ አንቱታ የሚቸረውና ክብር የሚገባው የጥበብ አድባር ቢሆንም በደፋር ብዕሩ ምክንያት የተውኔት ስራዎቹን ከቴአትር ቤቱ ከማገድ ባሻገር እንግልት ሲደርስበት መቆየቱን እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።
በመጨረሻም በቀድሞ የቴአትር ቤቱ አመራሮች አሻጥር ወከባ እንደተፈጸመበት በኋላም በጡረታ እንዲገለል ቢደረግም አርቲስቱ ግን በደሉን ችሎ በዝምታ መቆየቱን ተገልጿል።
የአሁኑ የቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ ማንያዘዋል እንደሻው ጌትነት ወደ ቤቱ እንዲመለስና ስራዎቹ ለተደራሲያን እንዲቀርቡ ጠይቋል።