ቀጥታ፡

በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እየታየ መምጣቱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

የካቲት 16/2012 (ኢዜአ) በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በፀጥታ ሃይሉ በተወሰዱ እርምጃዎች አንጻራዊ ሰላም እየታየበት መምጣቱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በደቡብና በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና የጸጥታ ችግሮች መታየት ከጀመሩ ሰነባብቷል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ እንዳሉት በአካባቢው የለውጥ እንቅስቃሴውን ለማደናቀፍ ላለፈው አንድ ዓመት የታጠቁ ሃይሎች ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

"ኦነግ ሸኔ" ብሎ ራሱን የሚጠራው ቡድን በአካባቢው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የጸጥታ አካላትን እስከ በመግደል መድረስ በአካባቢው ማህበረሰብ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል።

ታጣቂ ኃይሉ ባለሀብቶችን፣ ግለሰቦችን፣ የመንግስት አመራሮችና የጸጥታ ኃይል አባላትን ሳይቀር በመግደል በከተሞችና ገጠር አካባቢም በርካታ ጥፋቶችን አድርሷል።

ሆኖም መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ሊሳካ ሳይችል መቅረቱን አንስተዋል።

በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ወደ እርምጃ መግባቱን ኮሚሽሩ ገልጸዋል።

በምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞኖች፤ በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ታጣቂ ኃይሉ የሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

በመሆኑም የመንግስት የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመተባበር በታጣቂ ቡድኑ ላይ በተወሰደው እርምጃ አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ትብብርም አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ ጥሪ አቅርበዋል።

የካቲት 10 እና 11 ቀን 2012 ዓ.ም ጨፌ ኦሮሚያ አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄዱ ይታወሳል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጉባኤው ላይ የክልሉን የስድስት ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በደቡብና ምዕራብ ኦሮሚያ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በተወሰዱ እርምጃዎች ችግሩ እየተቃለለ መምጣቱን መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም