ቀጥታ፡

የፌዴራል ፖሊስ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው አለ

አዳማ፣ የካቲት 16/2012 (ኢዜአ) ህገ መንግስታዊ ታማኝነቱን ለማስጠበቅና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆናቸውን ፌዴራል ፖሊስ ዋና ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሸው ጣሰ ገለጹ።

ኮሚሽኑ በቢሾፍቲ ከተማ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

ኮሚሽነር ጄነራሉ በመድረኩ"በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችብሔር፣ ጎሳ፣ ወሰን፣ ኃይማኖትና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ነበሩ" ብለዋል።

ሆኖም የፖሊስ ሠራዊቱ በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማደረጉ በፀጥታ ዘርፉ የታየው ጠንካራ ጎን መሆኑንም አመልክተዋል።

በዚህም አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ ህገ ወጥነትና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ባለፉት ስድስት ወራት አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

በቀጣይም አስተማማኝ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል አባላቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነትና በሙሉ አቅማችው የሚንቀሳቀሱበት ወቅት መሆኑንም ተናግረዋል።

"ለተለያዩ የወንጀል ተግባር የሚውሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ፣ የሰዎችና የአደንዛዥ እፅ ዝውውር የተበረከተበት ወቅት ነበር" ያሉት ደግሞ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ መላኩ ፋንታ ናቸው።

ባለፉት ስድስት ወራት ከ420 በላይ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪዎችና  ከ104 ሺህ በላይ ተተኳሽ ጥይቶች በፌዴራል ፖሊስ ክትትል መያዛቸውን ገልጸዋል።

ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የጦር መሳሪያ ዝውውር በ71 በመቶ መጨመሩን ጠቁመው አሁንም የጦር መሳሪያ ዝውውር አሳሳቢ  መሆኑን አመልክተዋል።

በግማሽ የበጀት ዓመቱ  ከ1 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር፣ 42ሺህ ዩሮና የሌሎች ሀገራት ገንዘብን እንዲሁም ከ3 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር ከሀገር ሊወጣ ሲል መያዙንም አስረድተዋል።

በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ የውጭ ሀገር ገንዘብ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ተናግረዋል።

ከ560ሺህ ኪሎግራም በላይ ካናብስና ኮኬይን በቁጥጥር ሥር መዋሉን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ በዚህ የተሳተፉ 39 የውጭ ሀገራት ዜጎችና ስምንት ኢትዮጵያውያን ተይዞ ለህግ መቅረባቸውንም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በዩኒቨርሲቲዎች ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን ለማስቆም የፖሊስ አባላትን በመመደብ ተቋማቱ ከሁከትና ግጭት ማዕከልነት ወጥተው ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደታቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አብራርተዋል።

 ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ድሬደዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ መኮንኖች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም