የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ አዋጅ ኃላፊነት የጎደላቸውን አካላት ሥርአት ለማስያዝ ሚናው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ አዋጅ ኃላፊነት የጎደላቸውን አካላት ሥርአት ለማስያዝ ሚናው የጎላ ነው
የካቲት 16/2012 የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት የሚከለክለው አዋጅ ኃላፊነት የጎደላቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ሥርአት ለማስያዝ የራሱ ሚና እንደሚኖረው ተገለፀ።
የጥላቻ ንግግርን እና ሀሰተኛ መረጃን የሚከለክለው አዋጅ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ለፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ለአገራዊ አንድነትና ለሰብዓዊ ክብር ጠንቅ እየሆነ መምጣቱም እየተስተዋለ ነው።
ይኽው ድርጊት በህዝቦች ዘንድ ያሉ መልካም እሴቶችን በመሸርሸር ለአገር አንድነት ስጋት እየፈጠረ መሆኑም በተለያየ መድረክ ሲገለጽ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በማህበራዊ ሚዲያ እና በመደበኛ መገናኛ ብዙሀን የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች እያደረሱ ያሉት ጥፋት ከህግ ክፍተት ወይስ ከተቋማት የማስፈፀም ብቃት ማነስ ችግር? የሚሉትን ጉዳዮች አንስቶ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ በአዋጁ አስፈላጊነትና ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አንዷለም፣ የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ገብረጎዮርጊስ፣ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ እና የህግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም ታምራት ተካፍለዋል።
ተወያዮቹ በእዚህ ውቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ለአገሪቱ ሰላም እጦት እና ለአገር አንድነት ፈተና እየሆኑ መጥተዋል።
በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅ ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ፣ "በአገሪቱ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ በመሆናቸው ህጉን ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል" ይላሉ።
የጥላቻ ንግግርን እና ሀሰተኛ መረጃን የሚከለክል የህግ ማዕቀፍ የተዘጋጀው በሁሉም ክልሎች ጥናት ከተደረገና የተለያዩ አካላት በችግሩ ላይ ከተወያዩ በኋላ መሆኑንም አመልክተዋል።
የህግ ማዕቀፉን ለማዘጋጀት የበርካታ አገራት ልምድ እና ዓለም አቀፍ ህጎች ተሞክሮ መወሰዱን የጠቆሙት አቶ በላይሁን፣ የህግ ማዕቀፉ አገርን ለማዳን የግድ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ግልጽ የሆነ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ መልዕክቶች እየተሰራጩ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሩዋንዳና አውሮፓ አገራት በተለይም በጀርመን ደርሶ የነበረውን እልቂት ለአብነት ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህ ችግር መፍትሄ ለማስቀመጥ የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው አዋጁ በህገ መንግስቱ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስር የተቀመጠውን አንቀጽ 29 የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብትን የሚጣረስ እንዳየሆን የሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
"ህጉ የግለሰብ ነፃነትን በመጋፋት ለተወሰኑ ቡድኖች መብት ለማስጠበቅ የተዘጋጀ ነው" ሲሉ የህጉ መውጣት አላስፈላጊ ነው ሲሉም ተከራክረዋል።
በሌላ በኩል ለችግሩ መነሾ የህግ ክፍተት ሳይሆን የኢትዮጵያ አገረ መንግስት የመዳከም ውጤት በሚዲያ እና በሌሎች ተቋማት ለሚታየው የመዛነፍ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
የህግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም ታምራት በበኩላቸው ሰፊ ልዩነት ባለበት አገር ነፃነትና ደህንነትን በትክክል ማስተዳደር ካልተቻለ ወደ ቀውስ እና ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ይገልፃሉ።
የጥላቻ ንግግሮች በሂደት የቡድኖች የግጭት መነሻ በመሆን ለአገር ደህንነት ስጋት እንደሚፈጥሩ ጠቁመው "በተለይ በኢትዮጵያ ከመሀል ወደ ዳር ሲኬድ የመንግስት አስተዳደር እየሳሳ የሚመጣ በመሆኑ የሚያመጣው ውጤት የከፋ መሆኑን መረዳት ይገባል" ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ችግሩ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አይነት መልክ ያለው በመሆኑ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ህጉ አስፈላጊ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ያለው የወንጀል ህግ የጥላቻ ንግግርን እና ሀሰተኛ መረጃ በግለሰብ ደረጃ ሲፈፀም የሚያስቀጣ ቢሆንም ቡድኖች ላይ ቢፈጸም ህጉ ስለማያውቀው እንደማያስጠይቅ ገልፀው፣ ይህን ሁኔታ ለመቀየር የህግ ማዕቀፍ ማውጣት የግድ መሆኑን ተናግረዋል።
"መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ አስገዳጅ በመሆኑ የአዋጁ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም" ያሉት ደግሞ የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አንዷለም ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋና የዴሞክራሲ ልምምድ እንዲኖር በሚል በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት የሚያልፋቸው ጉዳዮች አሉ።
"መንግስት እርምጃ በመውሰድ በኩል ያለበት ለዘብተኝነት የሚያሳየው የችግሩ መሰረት መንግስት መሆኑን ሳይሆን የዜጎች መብትና ግዴታን ጠንቅቆ ከማወቅ አንጻር ነው"ብለዋል።
የህገ መንግስት ስርፀት ላይ በአግባቡ ባለመሰራቱ መብትን በሰፊው የመጠቀምና በአንጻሩ ግዴታን በአግባቡ ያለመወጣት ችግሮች ይታያሉም ነው ያሉት።
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በውጭ ሆነው ሲታገሉ የቆዩ መገናኛ ብዙሃን አገር ውስጥ ገብተው መስራት እንደጀመሩ አስታውሰው፣ አክቲቪስቶችን መንግስት ከማሰር ይልቅ በገባው ቃል መሰረት እንቅስቃሴያቸውን በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት እየያ መሆኑን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን አገር ውስጥ ከገቡም በኋላ በትግል ወቅት ሲሰሯቸው የነበሩ ሥራዎችን እንደሚሰሩና ይሄም መገራት እንዳለበት አንስተዋል።
እርስ በርስ የሚገፋፉ ፍላጎቶች ያሉበት አውድ በመሆኑ ነገሮችን በጥንቃቄ ማየት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው አዋጁ የጥላቻ ንግግርን ከመቆጣጠር አንፃር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተናግዋል።
የህግ ማዕቀፉ ክፍተት ቢኖርበትም ባለመውጣቱ ከሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ይልቅ በህዝቦች ዘንድ ያሉ መልካም እሴቶች እንዲጠናከሩ እና አንድነትን የሚያስጠብቅ በመሆኑ አስፈላጊነቱ እንደሚጎላ ተወያዮቹ አስምረውበታል።