ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃኑን መበራከት ለምርጫው መልካም እድል ውይስ ፈተና?

አዲስ አበባ የካቲት 16/2012 ኢዜአ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመገናኛ ብዙሃኑን መበራከት ለዘንድሮው ብሄራዊ ምርጫ ስኬታማነት ትልቅ እድል ሊሆን እንደሚችል ምሁራን ተናገሩ። 

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ የመገናኛ ብዙሃኑ ለህሊናቸው፣ ለሙያቸው፣ ለሃገር ጥቅምና ለህጉ ተገዥ ሆነው መስራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ ባካሄደችው አምስት ብሄራዊ ምርጫዎች ሚዲያዎቿ ምርጫን ከመዘገብ አኳያና መረጃን ለህዝብ ከማድረስ አንፃር ውስንነት ነበረባቸው ይላሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን።

ምክንያቱ ደግሞ በሃገሪቱ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃን ውስን መሆናቸውና ያሉትም ከፍተኛ የመንግስት ጫና ስለነበረባቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ።

እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ በህትመት ደረጃ ጥቂት የሚባሉ ጋዜጣና መፅሄት ቢኖሩም ብሮድካስት ላይ ግን  ምንም አይነት የግል ወይም የንግድ የሚባል መገናኛ ብዙሃን ያልነበረም።

በተለይ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ላይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየሰፋ የመጣውን የመረጃ ነፃነት ተከትሎ የመገናኛ ብዙሃኑ በቁጥርና በይዘት እየበዙ መምጣታቸውን የብሮድ ካስት ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት10 የህዝብ፣ 12 የንግድ፣ 50 የማህበረሰብ በአጠቃላይ 72 ሬዲዮ ጣቢያዎች ሲኖሩ ቅርንጫፎቻቸውን የሚጨምር ከሆነም እስከ 140 ይደርሳሉ።

ዘጠኝ የሚሆኑ የህዝብና 20 የግል ወይም የንግድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መኖራቸውም ታውቋል።

ሆኖም የመገናኛ ብዙሃኑ መበራከት በምርጫው ሂደት ህዝቡ የሚፈልገውን መረጃ በፍጥነትና በጥራት እንዲያገኝ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ምሁራኑ ይናገራሉ።

  እኔ ሁሉንም የምርጫ ሂደቶች  በጋዜጠኝነት  ተሳትፊያለሁ  ለህብረተሰቡ የተለየ መረጃ  እንዳልተሰጠው የሚናገረው ጋዜጠኛ የህግ ባለሙያና ጠበቃ ሳሙኤል ፍቅሬ ነው፡፡

"መገናኛ ብዙሃኑ እስከ ቅርብ ጊዜ አመታት ውስጥ በመንግስት ሞኖፖሊ ስር ነበር የነበሩት ፣አብዛኛው የግል መገናኛ ብዙሃን መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው በጣም የተገደበ እንደነበር ፣አቅማቸውም ተደራሽነታቸውም እንደዚሁ ክፍተት የነበረበት ነው፣አሁን ያሉትን መገናኛ ብዙሃን ባግባቡ ለመጠቀም መብቶቻቸውንም ለማስከበር የተደረጉት ማሻሻያዎች ቢኖሩም የሚለው ደግሞ  የህግና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ አቶ ሰለሞን ጎሹ ነው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን በቁጥር መበራከት እንደ መልካም አጋጣሚ ቢቆጠርም ህግና ስርአትን እንዲሁም ሙያዊ ግደታቸውን ተከትለው ካልሰሩበት ግን የስጋት ምንጭ ይሆናል ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት የመገናኛ ብዙሃኑ ወቅታዊ ሁኔታ በሁለት ፅንፍ የመሰለፍ፣ አንዳንዶቹ የመንግስትን ፍላጎት ብቻ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒ መቆማቸው ፈተና እንደሚሆንም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መገናኛ ብዙሃኑንና የመረጃ ነፃነትን የሚመለከቱ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን ማውጣቱ ለዚህ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም ምሁራኑ ጠቁመዋል።

ሆኖም እነዚህ የህግ ማእቀፎች ከምርጫ በፊት ተግባራዊ ካልሆኑ ችግሩ "ስር እየሰደደ" ይሄዳል የሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

የብሮድካስት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ እንዳሉት አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ከአሰራር አኳያ ተደጋጋሚ ስህተቶችን ይፈፅማሉ።

ሆኖም ባለስልጣኑ በምክር፣ ድጋፍና የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች ቁጥጥርና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሃኑ በኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው በመመራትና የአገሪቱን ህግ አክብረው ሊሰሩ ይባል ነው ያሉት።

የመገናኛ ብዙሃኑ ህግን በመተላለፍ የአገርንና የህዝብን ሰላም በማደፍረስ ላይ ከተጠመዱ ግን ባለስልጣኑ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም