የቮሊቦል ዳኞች ባለባቸው የአቅም ውስንነት ምክንያት ውድድሮችን በብቃት መምራት እየቻሉ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
የቮሊቦል ዳኞች ባለባቸው የአቅም ውስንነት ምክንያት ውድድሮችን በብቃት መምራት እየቻሉ አይደለም
የካቲት 15/2012 የአቅም ውስንነት የቮሊቦል ዳኞች ውድድሮችን በብቃት እንዳያመሩ እያደረጋቸው መሆኑ ተገለጸ። ስፖርታዊ ጨዋነትን በጣሰ መልኩ በዳኞች ላይ ስነምግባሩን ያልጠበቀ ተግባር የሚፈጽሙ የቮሊቦል ክለብ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች የእርምት እርምጃ መወሰድ አለበት ተብሏል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ለዳኞችና ኮሚሽነሮች ያዘጋጀው የማነቃቂያ ስልጠናና የምክክር መድረክ ዛሬ ሲካሄድ ዳኞች ያለባቸው የአቅም ውስንነት ችግር እንደሆነ ተገልጿል። ኢንተርናሽናል የቮሊቦል ኢንስትራክተር ትዕግስቱ ቀቀቦ ዳኞች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች የወጥነት ችግር እንዳለባቸው አመልክተዋል። የተጫዋቾችን ቦታ አያያዝ በአግባቡ የመረዳት፣ በውሳኔዎች ላይ ያለመናበብ፣ ቴክኒካል ስህተቶች ሲፈጸሙ ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት ችግሮች በዳኞች ላይ የሚስተዋል መሆኑን ገልጸዋል። በዳኞቹ ላይ ያሉ ክፍተቶች ዳኞች ጨዋታዎችን በራስ መተመንና በብቃት ጨዋታዎችን እንዳይመሩ እያደረገ መሆኑንና ዳኞች ያለባቸውን ችግር ማረም ይገባቸዋል ብለዋል። ብሔራዊ ዳኛ ትዕግስት ደንጊሶ በበኩሏ ዳኞች በየጊዜው አቅማቸውን ለሻል የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ ባለመሆኑ በፍጹም ሊሰሩ የማይገባቸውን ስህተቶች ሲሰሩ እንደሚታዩም ገልጻለች። በዳኞች መካከል እርስ በርስ የመነጋገርና የመማር ልማድ ማነስና አለመከባበር ችግርን መፍታት እንዳለባቸው ጠቁማ፤ የዳኞች ተናቦ መስራት የሚሰሩትን ስህተቶች እንደሚቀንስ ገልጻለች። የዳኞች ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ ቱካ የክለብ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች ቅሬታ የሚያቀርቡት ዳኞች ያለባቸውን የአቅም ክፍተት በማየት እንደሆነ አመልክተዋል። ይህ እንዳይፈጠር ዳኞች ራሳቸውን ብቁ አድርገውና ተዘጋጅተው መምጣት እንደሚገባቸው ገልጸዋል። የክለቦች አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾችና ቡድን መሪዎች ስፖርታዊ ጨዋነትን ጥሰው ዳኞችን ሲሳደቡና አጸያፊ ቃላት ሲጠቀሙ እንደሚታይ ገልጸው፤ አስፈላጊው ርምጃ ፌዴሬሽኑ እንዲወስድ ጠይቀዋል። ብቃትን መሰረት ያደረገ የዳኛ አመዳደደብና ቁሳቁሶችን ማሟላት እንደሚያስ ፈልግም የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል። የቮሊቦል ዳኞች ኮሚቴ አባል አቶ ፍርድአወቅ ደቻሳ ''በአገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ዳኞችና ኮሚሽነሮች ቢኖሩንም ጨዋታዎችን በብቃት እየመሩ ያሉት ውስን ናቸው'' ብለዋል። በዚህም ምክንያት በጨዋታዎች ላይ ዳኞች የሚመደቡት ለማዳረስ ሳይሆን የብቃት ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ገልጸው፤ ዳኞች አቅማቸውን በማጎልበት የብቃት ችግሩን እንዲፈቱ አሳስበዋል። በጨዋታዎች ላይ የሚመደቡ እያንዳንዱ ዳኞች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ዳኞችና ኮሚሽነሮች ያለባቸውን ችግር ራሳቸው አይተው መፍትሄ ለማምጣት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በጨዋታዎች ላይ የዳኞችና ኮሚሽነሮች ብቁና ዝግጁ ሆኖ መገኘት የሚፈጠሩ ስህተቶችን ለመቀነስ እንደሚያግዝም ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ ዳኞችና ኮሚሽነሮች አቅማቸው እንዲጎለብት ስልጠናዎችን እንደሚያዘጋጅም ተናግረዋል። ''ለጨዋታዎች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን የማሟላት ተግባር ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የሚያከናውነው ተግባር ነው'' ብለዋል። ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚጥሱ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች ላይ ፌዴሬሽኑ ጠንካራ ርምጃ እየወሰደ እንደሆነና ይሄም ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። በማነቃቂያ ስልጠናው ላይ ዳኞች በጨዋታ ወቅት በመሰረታዊነት ማድረግ የሚጠበቅባቸውና በሚሰሯቸው ስህተቶች ላይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።