ቀጥታ፡

በጎነት ላይ ኢንቨስት ያደረገ ሰው በህይወቱ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ፍሬ ማጨድ ይችላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 ( ኢዜአ) በጎነት ላይ ኢንቨስት ያደረገ ሰው በህይወቱ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ፍሬ ማጨድ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት "በጎነት ለአብሮነት" በሚል ሃሳብ ዛሬ በአፍሪካ ህብረት በተደረገ ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ማብሰሪያ መርሐ ግብር ላይ ነው። የአንድ ሰው በጎነት የሚገለጸው ለራስ መልካም በማድረግ ሲሆን ጊዜውን፣ ዕውቀትና ሃብቱን ሰውቶ ለሌላ ሶስተኛ ወገን በሚከፈል ሰናይ ግብር እንደሆነ ገልጸዋል። ለበጎ ፈቃድ የሚሰማሩ ወጣቶች በጎነት ላይ ኢንቨስት ያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ በጎነት መቸ የት እንደሆን ባይታወቅም በብዙ እጥፍ አብዝቶ እንደሚከፍል አስረድተዋል። በመሆኑም በጎነት ላይ ኢንቨስት የሚያደርግ ሰው በህይወቱ ትልቅ ትርጉም ያለው ፍሬ ማጨድ እንደሚችል ነው ያብራሩት። ''የትናንት ወጣቶች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ለአገር በመሰዋት ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው ቅርጽ እንድትይዝ ያስቻሉ ጀግኖች ናቸው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌሎችን ለማገዝ የሚደረገው የወጣቶች በጎነትም ትልቅ ጀግንነት ነው ሲሉ አመስግነዋል። ወጣቶቹ በቆይታቸው ውሏቸውን ከትልልቅ ሰዎች ጋር በማድረግ መልካምና ቅን ተግባርን እንዲፈጽሙ፣ መርጠው እንዲሰሙና እንዲያነቡ፣ ከራስ ወዳድነትና መንደርተኝነት ተላቀው አገርን ወደፊት እንዲያሻግሩ ጠይቀዋል። በወጣቱ ውስጥ ከፍተኛ እምቅ ኃይል እንዳለ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ይህን ኃይል በጥበብ፣ በእውቀትና በብልሃት ከተጠቀሙበት ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ እንደሚያወጣት ገልፀዋል፡፡ ወጣቶች በሕይወት ዘመናቸው በሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ሳይበገሩ በጽናት መራመድና ከግብ መድረስ እንዳለባቸውም ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ያጋጠማቸውን የሕይወት ተሞክሮ በማንሳት መክረዋል። "ወጣትነት አበባና እሳት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወጣቶች ሃይላቸውን በብልሃት ተጠቅመው ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና መውሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል። ወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ካልተቻለ ግን የወጣትነት እሳት ባህሪ አገር እንደሚያወድም ገልፀው፤ የወጣትነትን ወንዝ ገድቦ አገር ማልማትና በጥበብ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊያን የቆዬ የመረዳዳት ባህል ነባር እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን ገልጸው፤ ወጣቶች በሚሰማሩባቸው ጊዜ እሴቶችን በማዳበር እንዲሰሩና በቸር እንዲመለሱ ተመኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም