የህግ የበላይነትን ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው -ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

75
ደሴ  የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የህግ የበላይነትን በአስተማማኝ ደረጃ ለማስፈን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን አስታወቁ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ባሴሩ አካላት ዘንድ ስርዓት አልበኝነት እየተስተዋለ ይገኛል ። ይህን ችግር ለመቀልበስም ህዝቡን በባለቤትነት በማሳተፍ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ከመቼውም ጊዜ የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ስርዓተ አልበኝነት እንዲነግስ አበክረው በሚሰሩ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል አደርጎ በመለየት ለህግ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። የመጣው ለውጥ የሃገሪቱን ብልፅግና እንዲያረጋግጥም የህዝቡ ብርቱ ድጋፍና እገዛ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል ። ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ሰላምን በማስፈን ልማቱ እንዲፋጠን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አቶ ደመቀ መኮንን አሳስበዋል። በተለይም ወቅቱ የአፈርና ውሃ ልማትና ጥበቃ ስራ የሚከናወንበት ወሳኝ ሰዓት በመሆኑ ያለሙ መሬቶችን በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ የህዝቡ ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት ብለዋል ። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ደህንነት በመጠበቅ በየደረጃው በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ። በክልሉ አልፎ አልፎ ብጥብጥ እንዲፈጠርና ልማቱ እንዲደናቀፍ የሚጥሩ አካላትንም ህብረተሰቡ ከእኩይ ተግባራቸው ሊያስቆማቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል። "ወሎ የሰላም፣ የፍቅርና የመቻቻል ዞን ነው " ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ፤ ይህንኑ ምሳሌነት በመጠበቅ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና መሰል ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል። ህብረተሰቡ ከቂም በቀልና ከጥላቻ ተላቆ እያንዳንዱን ጥያቄ በሰከነና በሰለጠነ አግባብ ከማቅረብ በዘለለ የመፍትሄውም አካል ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባ አብራርተዋል። በውይይቱ እየተሳተፉ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች በውይይቱ ላይ  የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ፣ የመብራት፣ ስልክና ሌሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጥያቄ አቅርበዋል ። በውይይቱ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከህብረተሰቡ እየተነሱ ለሚገኙ ጥያቄዎች አመራሩ ምላሽ በመስጠት ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ርዕሰ መስተዳደሩ ከሰዓት በፊት በአካበቢው የተገነቡ የድልድይ፣ የሆስፒታልና የኮሌጅ መሰረተ ልማቶች ምረቃ ማካሄዳቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም