ቱርክ 4 የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች ወደ ሶሪያ እንዳይገቡ አገደች

103
የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) ቱርክ የአየር ክልሏን አልፈው ሶሪያ ሊገቡ የነበሩ ሁለት ቦምብ ጣዮችን ጨምሮ አራት የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች ማገዷን የሩሲያውን ተነባቢ ጋዜጣ ነዛቪ ሲማያን ዋቢ አድርጎ ሚድል ኢስት ሞኒተር  ዘግቧል። በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ የሚካሄዱ ጦርነቶች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን የሚያመላክቱ ነገሮች መኖራቸውን ተከትሎ ሩሲያ በቦታው ያላትን ወታደራዊ ይዞታ ሊያጠናክሩ የሚችሉ የጦር አውሮፕላኖች እንደነበሩም በዘገባው ሰፍሯል፡፡ ምንጮች ነግረውኛል ያለው ዘገባው  ለስትራቴጅክ ውጊያ የሚያገለግሏትን የሩሲያ ዘመናዊ ታንኮች፣ የሚሳይል አውሮፕላኖች፣ የከባድ ጭነት መርከቦች፣ ከባድ የጦር መሣሪያዎች እና ፀረ-የጦር መሣሪያ በከባድ ጭነቶች ወደ ቦታው መድረሳቸውን ገልጿል፡ ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያ ታንክና ወታደር የሚሸከሙ ማሽኖችና ምሽግ ለመገንባት ብሎም መሰናክሎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችን ያካተተ ወታደራዊ ማጠናከሪያ እያከናወነች መሆኗን በዘገባው ተገልጿል፡፡ ቱርክ ይህን እርምጃ የወሰደችው ኢድሊብና አሌፖ በተሰኙ የሶሪያ  ግዛቶች ላይ የሩሲያ የጦር ሃይል በሚወስደው እርምጃ ግጭቶች እየተባባሱ በመምጣታቸው ጉዳዮን በሚመለከት የአንካራና ሞስኮ ባለስልጣናት ከስምምነት መድረስ ባለመቻላቸው ሳቢያ መሆኑን ሚድል ኢስት ሞኒተር በገፁ አስፍሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም