ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰላለፍ አሁንም የሰከነ መነጋገርና መተቻቸት አይታይበትም

 አዲስ አበባ የካቲት 14/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰላለፍ አሁንም የሰከነ መነጋገር፣ መተቻቸትና መቀራረብ የራቀው መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር  ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ባዘጋጀው መድረክ የብልጽግና፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲና የአማራ ማህበራዊ ራዕይ ግንባር አመራር አባላት ዛሬ በህግ የበላይነት ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የአገሪቷ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፍ በሰከነ መልኩ ተቀራርቦ በመነጋገርና በመተቻቸት ለአገር የሚጠቅም ሥራ ከመስራት ይልቅ በልዩነቶች ላይ ጊዜ እንዲያባክኑ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአማራ ማህበራዊ ራዕይ ግንባር የተወከሉት አቶ ስዩም መንገሻ እንደሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ባለው አሰላለፍ ከመቀራረብ ይልቅ በልዩነቶች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።

ይህ ደግሞ መንግስትን ህግ ለማስከበር እርምጃ ሲወስድም ሆነ ነገሮችን በትዕግስት ሲያልፍ እንዲወቀስ እያደረገው ነው ብለዋል።

"በአገሪቷ የህግ የበላይነት ተረጋግጦ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከተፈለገ ፓርቲዎች ተቀራርበው መወያየትና መደጋገፍ ይኖርባቸዋል" ነው ያሉት።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቃርኖ ሀሳቦች በውይይት እንዲረግቡ ለማድረግ መንግስት መድረኮችን ማመቻቸት እንዳለበትም አቶ ስዩም ጠቁመዋል።

የህግ የበላይነትን እውን ለማድረግ የውይይት አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመው "ይህ ካልሆነ የህግ ጥሰት እየተበራከት የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ እየገባ ይሄዳል" ብለዋል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ሴናፍ ጎንፋ በበኩላቸው "የህግ የበላይነት መሰረት እየያዘ የሚመጣው የህዝብ የመደራጀት፣ የመናገርና የመሰብሰብ ነፃነት እውን ሲሆን ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ብዙ መገፋፋት፣ ሸፍጥና ማጭበርበር የሚስተዋልበት እንደነበር አስታውሰው ይህም አሁን እየተፈጠረ ላለው የህግ ጥሰት አይነተኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቷ በህዝብ ግፊትና ፍላጎት ወደ ኃላፊነት በመጣው የለውጥ አመራር በትጥቅ ትግሉ የነበሩም ሳይቀሩ ለሠላማዊ ትግል አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም በመንግስትና በእነዚህ ተፎካካካሪ ፓርቲዎች መካከል የተደረሰው ስምምነት ምን እንደሆነ ለህዝብ ግልፅ ሳይሆን እስካሁን መዝለቁን ጠቅሰዋል።

"ይህ መሆኑ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እዚህም እዚያም ለሚታዩ ግጭቶችና የህግ ጥሰቶች አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል" ነው ያሉት።

የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ አቶ ሃጎስ ወልደኪዳን በበኩላቸው ለሚፈጸሙት የህግ ጥሰቶችና ጥፋቶች ዋናው ምክንያት ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋም መፍጠር አለመቻሉ ነው ይላሉ።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ትኩረታቸው የሃሳብና የፖሊሲ ክርክር ላይ ሳይሆን ልዩነት በሚፈጥሩ ጥቃቅን ሃሳቦች ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም ህዝቡን ከማቀራረብና ለህግ ተገዥ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግጭት መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ነው የተናገሩት።

ለአገሪቷ ሕዝቦች የመጣው ለውጥ "ትግራይ አልደረሰም" ያሉት አቶ ሃጎስ በክልሉ ውጥረት እንጂ የተረጋጋ ሠላም እንደሌለ ገልጸዋል።

የህግ ምሁሯ ወይዘሮ አበበች ሞሲሳ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን እውን ለማድረግ መንግስት፣ ግለሰብም ይሁን የፖለቲካ ፓርቲ ህግ አክብረው መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል።

በተለይም ወጣቶች ለህዝባዊ ዓላማ ስኬት ከመቆም ይልቅ የጥፋት መሳሪያ እንዳይሆኑ መክረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላቱ ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶች በፖለቲካ ፓርቲ ወይም በሌሎች የሲቪል ማኅበራት በመደራጀት ለገራቸው ሠላም፣ ልማትና ብልጽግና እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም