የአማራ ክልል የሀገር አቀፉ አጠቃላይ የባህል ስፖርት ውድድር አሸናፊ ሆነ

110
ደብረ ማርቆስ፣ የካቲት 14/2012(ኢዜአ) በደብረ ማርቆስ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ሃገር አቀፉ የባህል ስፖርቶች ውድድር በአማራ ክልል አጠቃላይ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ። ከየካቲት 7/ 2012 ዓ.ም  ጀምሮ 17ኛው  የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድር እና 13ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌስቲቫል ሲካሄድ ቆይቷል። በባህል ስፖርት  ወድድር በአጠቃላይ ውጤት የአማራ ክልል አንደኛ በመወጣት 12 ዋንጫዎችን ሲያገኝ ትግራይ ክልል ደግሞ  በሦስት ዋንጫዎች ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል። በባህል ስፖርት ፌስቲቫል በተደረገው ውድድር ደግሞ ደቡብ  አንደኛ፣ አማራ ክልል ሁለተኛ እና ትግራይ ሶስተኛ  በመውጣት  አሸናፊ ሆነዋል። በውድድሩ በስፖርታዊ ጭዋነት በባረከተው አስተዋጽኦ ደበብ ክልል የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል። የኢትዮጵያ  ባህል ስፖርቶች ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት ኢንጅነር ሰለሞን አስፋ በውድድሩ ማጠቃለያ እንዳሉት ስፖርት አንድነትን፣ ሰላምን ፍቅርን እና ወንድማማችነትን የሚያጎለብት ነው። "ባህል ስፖርት ውድድሩ የጥንት የማንነት መገለጫ የሆኑ የባህል ስፖርቶች በወጣቱ ዘንድ እንዲዘወተሩና እንዳይጠፉ ለማገዝ የተዘጋጀ ነው "ብለዋል። ከተሳታፊዎች መካከል ከትግራይ ክልል የትግል ተጫዋች የሆነችው ወጣት ራሄል ስዩም በበኩሏ በውድድሩ አሸናፊና ተሸፊፉ ከመለየቱ ባለፈ የእርስ በእስር ግንኙነትን ለማጠናከር የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግራለች። በደብረማርቆስ ቆይታዋም በጣም ጥሩ ጊዜ ከማሳለፏም ባለፈ የማይረሱ ጓደኞችን ማፍራት እንደቻለች ገልጻለች። ከአፋር ክልል የባህል ስፖርት ፌስቲቫልን ለማሳየት የተገኘው ወጣት አኽሎም መሀመድ ውድድሩ የአንዱን ባህል አንዱ እንዲያውቅ እንዲሁም ባህልን ለማስፋፋት ማገዙን ተናግሯል። ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች የምስክር ወረቀትና ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል። በውድድሩ ከሁለት ሺህ በላይ የስፖርት ልኡካን ቡድን አባላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም