ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና እስራኤል ታሪካዊ ትስስር በምጣኔ ሀብትም መደገም እንዳለበት ተገለጸ

  አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2010  ኢትዮጵያና እስራኤል ያላቸውን የሁለትዮሽ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ማጎልበት እንደሚጠበቅ የአገሮቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ገለጹ። በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉበኝት እያደረጉ ካሉት ከእስራኤል ፕሬዚዳንት ሬውቨን ሪቭሊን ጋር የመጣው 30 አባላትን የያዘው የንግድ ልዑክ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ዛሬ መክሯል። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ከጥንት ጀምሮ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሁለቱ አገሮች በምጣኔ ሀብት ረገድ ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ማጎልበት ያስፈልጋል። 'ኢትዮጵያ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ሰፊ የሰው ሃይል ባለቤት ናት' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኩባንያዎች በማምረቻው ዘርፍ፣ በመድሃኒት፣ በጤና፣ በግብርና ውሃ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ኃይልና ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ የሚያደርጋቸው ዕድሎች እንዳሉ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና የግብርና ምርቶች ማቀነባባሪያ ፓርኮች መገንባቷን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ከሰሃራ በታች አገሮች መካከል ተመራጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆን ያስቻላት የተሻለ ፖሊሲና መሰረተ ልማት እንዳላት ጠቅሰዋል። በማምረቻ ዘርፍ ቢሰማሩ ከአገር ውስጥ ሰፊ የገበያ ፍላጎት ባሻገር፤ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል የነጻ ዓለም አቀፋዊና ክፍለ አህጉራዊ ሰፊ የገበያ ዕድል እንዳለ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለአጎራባች አገሮች ኃይል ማቅረብ ላይ መሰማራቷን የገለጹት ዶክተር አክሊሉ፤ በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ተመራጭ የኢንቨስትመንት ዕድል ያላት በመሆኑ የእስራኤል ኩባንያዎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሰፊ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸው፤ እስራኤል በዘርፉ ባላት ልምድ የዕውቀት ሽግግር እንዲፈጠር ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል። በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዘርፍ ዳይሬክተር ጄኔራል ራቪያ ዛዶክ በተወካያቸው ባስተላለፉት መልክት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሁለቱ አገሮች መሪዎች የሚያደርጓቸው ጉብኝቶች የሁለትዮሽ ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዲጎለበት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የመንግስታቱ የጸጥታ ምክር ቤት አባልነቷ፣ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በእስራኤል መኖራቸው፣ ለአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷ ከሌሎች አገሮች በተለየ የሁለቱ ግንኙነት እንዲጎለብት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ስለሆነም አገሮቹ ለዘመናት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በምጣኔ ሀብት ትስስር ማጎልበት ይገባቸዋል' ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ኩባንያዎች እንዲመጡ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገለጸው፤ እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላትን አቅም ወደ ኢትዮጵያ ማሸጋገር የምትፈልግ መሆኗንም ጠቁመዋል። እስራኤል በአፍሪካ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በበርካታ ታሪካዊ ምክንያቶች ለእስራኤል ጠቃሚና ቀዳሚ መዳረሻ እንደሆነች ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዷ የያዘቻቸው ግቦች ስኬትም እስራኤል ከጎን ትቆማለች ብለዋል። በኢትዮጵያ ወደ 1 ቢሊዮን ከ112 በላይ በግንባታና በማምረት ጅምር ላይ የሚገኙ ወደ 112 የሚጠጉ የተለያዩ ፕሮጀክት ያሉ ሲሆን የኢንቨስትመንት መጠናቸውም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ዶክተር አክሉሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም