ለድብልቅ የማርሻል አርት ስፖርት ድጋፍ ቢደረግ የገቢ ምንጭ አማራጭ መሆን ይችላል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012  መንግስትና ባለሀብቶች ለተደባለቀ የማርሻል አርት ስፖርት ድጋፍ ቢያደርጉ ለአገሪቷ የገቢ ምንጭ አማራጭ መሆን እንደሚችል በዓለም መድረክ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ተወዳዳሪዎች ገለጹ። የተደባለቀ የማርሻል አርት የቦክስ፣ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ጁዶ፣ ዉሹ፣ ኪክ ቦክስ፣ ትግል እና ሌሎች የድብድብ ስፖርት አይነቶችንና የአጨዋወት ስልታቸውን አጣምሮ የያዘ ነው። ኡመር ጀማል ወደ ተደባለቀ የማርሻል አርት ስፖርት ከመግባቱ በፊት በኪክ ቦክሲንግና በትግል ውድድሮች ይሳተፍ እንደነበር ያወሳል። ከሰባት ዓመት በፊት ወደ ስፖርቱ እንደገባና እስካሁን ባደረጋቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ሽንፈት እንዳልገጠመውም ገልጿል። ለስፖርቱ ጥልቅ ፍቅር እንዳለውና የሚወዳደረውም ህይወቱን ለመምራት እንደሆነም ነው የሚናገረው ኡመር። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደባለቀ የማርሻል አርት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያንቀሳቅስ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹም በዓመት በአማካይ ከ34 እስከ 138 ሺህ ዶላር ያገኛሉ። እንደ ኡመር ገለጻ ፤ ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የስፖርቱ እንቅስቃሴ የለም በሚባል ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን አሁን ጅምር እንቅስቃሴ እየታየ ነው። ይህ ስፖርት እያደጉና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እያስገኙ ከሚገኙ ስፖርቶች አንዱ እንደሆነም ተናግሯል። ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲካሄዱ ስፖንሰር ቢያደርጉና ስፖርቱን ቢያስተዋውቁ ተወዳዳሪዎች ከሚያገኙት ገንዘብ ባሻገር እነሱም ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ አመልክቷል። በተወዳዳሪዎች የኢትዮጵያ ቆይታም አገሪቷ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ነው ኡመር የገለጸው። ተወዳዳሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም ስፖርቱ እንዲያድግ አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ተናግሯል። በኢትዮጵያ ስፖርቱን የገቢ ምንጭ ለማድረግ ጊዜው ገና ቢሆንም ከስፖርቱ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በፍጥነት ለማግኘት ብቁ ተወዳዳሪዎችን ማፍራትና የስፖርት ማዘውተሪያ ቁሳቁሶችን ሟሟላት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል። የተደባለቀ ማርሻል አርት ክለቦችን የማቋቋምን ጉዳይ መንግስትና የግል ባለሀብቶች ትኩረት እንዲሰጡትም አመልክቷል። ሌላኛው የስፖርቱ ተወዳዳሪ ሽፋ ሀሰን ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ስፖርቱ እንደገባና በተለያዩ አህጉር አቀፍ ውድድሮች እንደተሳተፈ ገልጿል። በሌሎች አገራት ስፖርቱ ለተወዳዳሪዎች የገቢና የስራ እድል መፍጠሪያ እንደሆነና አገራትም ከማስታወቂያ ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሷል። በመጪው ግንቦት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ውድድር በኢትዮጵያ መካሄዱም ስፖርቱን ከማስተዋወቅ ፋይዳው ባሻገር አገሪቷ ከማስታወቂያና ከስፖንሰሮች ገቢ ማግኘት የምትችለበት ዕድል እንደሚፈጠር ገልጿል። የተደባለቀ ማርሻል አርት የቢዝነስ ወይም የገቢ ማግኛ ስፖርት እየተባለ እንደሚጠራና ኢትዮጵያም ለስፖርቱ ተገቢውን ትኩረት ሰጥታ ከሰራች ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ነው ሽፋ የገለጸው። ሌላኛ ተወዳዳሪ ተድላ ተሰማ የተደባለቀ ማርሻል አርት ስፖርት በኢትዮጵያ ቢያድግ ተወዳዳሪዎች በሚያገኙበት ገቢ አገራቸውንም ይጠቅማሉ ነው ያለው። ኢትዮጵያም ስፖርቱን በአግባቡ መምራት የሚያስችል ስርዓትና ስትራቴጂ ከነደፈች ከስፖርቱ የጥቅም ተቋዳሽ መሆን እንደምትችል ጠቁሟል። ስፖርቱ ለኢትዮጵያ አዲስ እንደመሆኑ ለዕድገቱ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት፣ ብቁ ዳኞችና አሰልጣኞችን እንዲኖሩ ማድረግና የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት አለባቸው ብሏል። ኢትዮጵያዊያኑ ተወዳዳሪዎች በዩናይትድ አፍሪካ ኤምኤምኤ አዘጋጅነት ግንቦት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የተደባለቀ የማርሻል አርት ውድድር ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩና አቅማቸውንም ማሳየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም