በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የተደባለቀ የማርሻል አርት ውድድር ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የተደባለቀ የማርሻል አርት ውድድር ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የተደባለቀ የማርሻል አርት ውድድር ከግንቦት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የውድድሩ አዘጋጆች ውድድሩን አስመለክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የተደባለቀ የማርሻል አርት የቦክስ፣ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ጁዶ፣ ውሹ፣ ኪክ ቦክስ፣ ትግል እና ሌሎች የድብድብ ስፖርት አይነቶችንና የአጨዋወት ስልታቸውን አጣምሮ የያዘ ነው። መቀመጫውን በካናዳ ኤድመንተን ከተማ ያደረገው የተደባለቀ የማርሻል አርት ውድድሮች አዘጋጅ ዩናይትድ አፍሪካ ኤም.ኤም.ኤ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ጸጋዬ ውድድሩ የተዘጋጀው ኢትዮጵያን የአፍሪካ ማዕከል በማድረግ ስፖርቱን ለማስፋፋት መሆኑን ገልጸዋል። በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ከአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አገሮች የተውጣጡ በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ያደረጉ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉ የተደባለቀ የማርሻል አርት ተወዳዳሪዎች ኡመር ጀማል፣ ሽፋ ናስር፣ ቢንያም ሽብሬና ተድላ ተሰማ መሆናቸው ታውቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደባለቀ የማርሻል አርት ውድድሮች የሚካሄዱት ከ52 እስከ 120 እና ከእዚያ በላይ ኪሎ ግራም ክብደት ባላቸው ሰዎች ተከፋፍሎ ነው። እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ፤ በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ ፕሮፌሽናል የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች በተጨማሪ ሌሎች ተወዳዳሪዎች አስፈላጊውን የክብደት መጠን ካሟሉ በውድድሩ ላይ መሳተፍ ይችላሉ። ውድድሩ በኢትዮጵያ ስፖርቱን ለማስተዋወቅና በቀጣይም ለማስፋፋት እንደሚያግዝና በአፍሪካ ስፖርቱን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል። "ተቋሙ እስካሁን ውድድሮችን ሲያዘጋጅ የነበረው ካናዳ ውስጥ ብቻ እንደነበረና አፍሪካ ውስጥ ሲያዘጋጅ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ናት" ብለዋል። ዩናይትድ አፍሪካ ኤምኤምኤ በኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ወደኢትዮጵያ ቢመጣም ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ ውድድሩ እስካሁን እውቅና እንዳያገኝ ማድረጉን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የኪክ ቦክሲንግ አደረጃጀት ኮሚቴ በመቋቋሙ ከኮሚቴው ጋር በመሆን ውድድሩን ለማዘጋጀት በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከውድድሩ ቀደም ብሎ ዩናይትድ አፍሪካ ኤም.ኤም.ኤ ዓለም አቀፍ የስፖርቱ ዳኞችን ወደኢትዮጵያ በማምጣት ለዳኞች ስልጠና እንደሚሰጥም ገልጸዋል። አቶ ኢሳያስ ለተወዳዳሪዎች ከፍ ያለ ሽልማት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳዊት ትርፉ በበኩላቸው ውድድሩ እስካሁን ያልተካሄደው ለስፖርቱ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆንና የቁርጠኝነት ማጣት መሆኑን ገልጸዋል። ኮሚሽኑ ለውድድሩ የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት ሥራ ከውድድሩ አዘጋጅ ዩናይትድ አፍሪካ ኤምኤምኤ ጋር በጋራ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የስፖርት ኮሚሽኑ ለውድድሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ስፖርቱ በመዲናዋ እንዲዘወተር ቅድሚያ የማስተዋወቅና የማስፋፋት ሥራ ለመስራት ማቀዱን አመልክተዋል። በአገር አቀፍ ደረጃም ስፖርቱ እንዲታወቅና እንዲስፋፋ ግፊት እንደሚያደርግ አክለዋል። "የውድድሩ መካሄድ ስፖርቱን ከማሳደግ ባለፈ ለገጽታ ግንባታ ወሳኝ አስተዋጽኦ አለው" ብለዋል። የአዲስ አበባ የኪክ ቦክሲንግ አደረጃጀት ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ሞቲ ሞረዳ የውድድሩ መዘጋጀት ስፖርቱ በመዲናዋና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲዘወተር በር እንደሚከፍት ገልጸዋል። ሦስቱ የውድድሩ አዘጋጅ አካላት ውድድሩን በቅንጅት ለማካሄድ የሚያስቸላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል። የተደባለቀ ማርሻል አርት የውድድር አይነት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ648 ዓመተ ዓለም "ፓንክራቲዮን" በሚል ስያሜ እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ስፖርቱ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ እያደገ እንደመጣና በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኙ ካሉ ስፖርቶች መካከል ይጠቀሳል።