በአሶሳ ከተማ በዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ 46 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

58
አሶሳ ፣የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) በአሶሳ ከተማ በተደራጀ መልኩ የዘረፋ ወንጀል ሲፈጽሙ ነበሩ ተብለው የተጠረጠሩ 46 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የከተማዋ ፖሊስ ገለፀ ። በከተማው አስተዳደር ፖሊስ  የወንጀል መከላከል ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ዋና ኢንስፔክተር ደረጃ ኢታና  ለኢዜአ እንደገለፁት የህብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ግብረ ኃይል ተቋቁሟል ። ግብረ ኃይሉ ህብረተሰቡ የሰጠውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ ትናንት ምሽት 45 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል ። ግለሰቦቹ በተደራጀ የዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው ተብሏል ። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በሥነ-ምግባርና ሌሎች ችግሮች ከፀረ- ሽምቅ ፣ ከመደበኛ ፖሊስና ከሌሎች የጸጥታ አባልነት የተሰናበቱና የተደራጀ የዘረፋ ቡድኑን በበላይነት ሲመሩ እንደነበር ማስረጃ የተገኘባቸው ናቸው ። ተጠርጣሪዎቹ የግለሰቦችን ቤት በመስበር የዘረፉት ፍርጅ፣ ቴሌቪዥንና ሌሎች የቤት ቁሳቁሶች በኢግዚቪትነት እንደተያዙ አመልክተዋል። ሌላ አንድ ግለሰብ ደግሞ ዛሬ ረፋድ ላይ በከተማው ወረደ 1 ቀጠና 4 የግለሰብ ቤት በመስበር 3 ሺህ 587 ጥሬ ገንዘብ  ዘርፎ ሊሰወር ሲል እጅ ከፍንጅ መያዙን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ አስፈላጊው ምርመራ ከተካሔደ በሃላ ፈርድ ቤት የሚቀርቡ መሆኑን የገለጸው ኢንስፔክተር ደረጀ ህብረተሰቡ ከግብረ ሃይሉ ጎን ተሰልፎ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም