ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሰለፍ ለውጡን እንደሚደግፉ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሰለፍ ለውጡን እንደሚደግፉ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ሀዋሳ፤ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጎን በመሰለፍ ሀገራዊ ለውጡንና የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት እንደሚሰሩ የሀዋሳና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ነዋሪዎቹ ለውጡን በመደገፍ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ሰልፍ አካሄደዋል።
ከድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዮሴፍ ሀማሮ በሰጡት አስተያየት "ዶክተር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በርካታ ለውጦችን እያየን ነው" ብለዋል፡፡
የሲዳማ ህዝብም እንዲሁ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ በዴሞክራሲዊ መንገድ ምላሽ ያገኘው በዚሁ የለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነም አስታውሰዋል ፡፡
"ይህ ለውጥ ከዳር እንዲደርስ የህዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል "ያሉት አቶ ዩሴፍ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አንቺንአሉ አሰፋ በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ የዜጎች ዴሞክራሲዊና ሰብዓዊ መብቶች በትክክለኛው መንገድ መከበር መጀመሩን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥና በአመራርነት ደረጃም በርካታ ሴቶችን ወደ ሥልጣን በማምጣት ተምሳሌታዊ ተግባራትን ማከናወናቸውን አመላክተዋል።
በሀገር ደረጃ የተጀመሩት ሁለንተናዊ ለውጦች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከዶክተር ዐብይ ጎን በመሰለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት በሀገሪቱ እንዲሰፍን በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ በሀገሪቱ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲከበር፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሠላማዊ ትግል የሚያካሂዱበት ሰፊ ምህዳር እንዲፈጠር ፣በሀገራት ዕርቅ እንዲወርድ ፣የአካልና የሕሊና እስረኞች ነፃ እንዲወጡም ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በህብረ-ብሔራዊነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ጥራቱ " ልዩነቶችን በማጥበብ በመደመር እሳቤ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል "ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣ በርካታ አንፀባራቂ ድሎች መገኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ ናቸው።
ዘመናትን ያስቆጠረው የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መልስ ያገኘው በዚሁ የለውጥ ወቅት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
"የሲዳማ ህዝብና አብረውት የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ለለውጡ መሪ ያሳዩት ድጋፍ ለማደናቀፍና አካባቢውን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ለሚጥሩ ኃይሎች በቂ ምላሽ የሰጠ ነው" ብለዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ በሀዋሳና አካባቢው የሚኖሩ ወጣቶች፣ ሴቶች፣የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።