ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ በመጪው እሁድ በባህር ዳር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ ነው

ባህር ዳር ሰኔ 20/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በማካሄድ ላይ ያሉትን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ የፊታችን እሁድ በባህርዳር ከተማ የድጋፍ ሰልፍ  እንደሚካሄድ የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ። የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወጣት ኃይሌ አድማሱ እንደገለጸው የድጋፍ ሰልፉን ማድረግ ያስፈለገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላመጡት ለውጥ ለማመስገንና ለወደፊት ስራቸውም የባህርዳር ህዝብ ከጎናቸው መሆኑን ለመግለጽ ነው። የድጋፍ ሰልፉን የሚያስተባብሩ ሰባት ዋናና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግሯል። በከተማዋ የሚካሄደው ሰልፍ በተሳካና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሁሉም የከተማዋና አካባቢው ነዋሪ ህዝብ  ድጋፉን የሚገልጽበት መሆኑን የተናገረው ደግሞ የአቢይ ኮሚቴው አባል ወጣት ልዑል ብርሃኑ ነው። የድጋፍ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅም አስተባባሪ ኮሚቴው የከተማው ወጣቶችን አደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ ወጣቱም ሆነ ህዝቡ የድጋፍ ሰልፉ ባለቤት ሆኖ እንደሚሰራም አስረድቷል። ሰልፉ በባህርዳር ብሄራዊ ስታዲየም ከጥዋቱ 12 ሰዓት ተጀምሮ አምስት ሰዓት ላይ የሚጠናቀቅ መሆኑንም የሰልፉ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡ በሰልፉ ላይ ከ300 ሺህ በላይ ህዝብ ይታደማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያስመዘገቡት ያለውን ውጤት ለማመስገን የተቋቋመውን የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ያቀረበውን ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩ ተቀብሎታል። የተጀመሩ ለውጦች ቀጣይነት እንዲኖራቸውም አስተዳደሩ ከመላው የከተማው ህዝብ ጋር ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይም ዘርን፣ ቀለምንና የፖለቲካ አመለካከትን በማይነካ መልኩ ወጣቱም ሆነ ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው በበኩላቸው ሰኔ 24 በባህርዳር የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። የሰላሙ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ወጣቱና የከተማው ነዋሪ ህዝብም ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ከፀጥታ አስከባሪው ጎን እንዲሰለፍም አሳስበዋል። ወጣቱም ሆነ ሌላው ህብረተሰብ በሰልፉ ወቅት የተለየ ነገር ሲመለከት ፈጥኖ ለፀጥታ አስከባሪ አካላት እንዲጠቁምም ኮማንደር ዋለልኝ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም