የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉበትን መዋቅራዊ ችግሮች በመፍታት ተቋማዊ አቅሙን እያጠናከረ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉበትን መዋቅራዊ ችግሮች በመፍታት ተቋማዊ አቅሙን እያጠናከረ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉበትን መዋቅራዊ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት በሚወስደው ማሻሻያ ውጤት እያመጣና ተቋማዊ አቅሙን እያጠናከረ መሆኑን ገለጸ። የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በተሻለ መልኩ እንዲወጣ በድጋሚ ተቋቁሟል። በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ፤ የሕግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ተግባር አላማ አድርጎ ተቋሙ እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪም ተቋሙ በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በመንግስት ተቋማት ውስጥ የመረጃ ነጻነት መብት እየተከበረ መሆኑን የማረጋገጥና የመቆጣጠር ሃላፊነትም ተሰጥቶታል። ተቋሙ የተሰጠውን ሃላፊነት ለመወጣት መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ ለኢዜአ ገልጸዋል። ልማዳዊ የሆነ የመረጃ አያያዝና ዘመናዊ የሆኑ የአሰራር ስልቶችን አለመከተል ዜጎች አቤቱዎችን ወደ ተቋሙ ይዘው በሚመጡበት ሰአት በአግባቡ እንዳይስተናገድ ያደረገ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል። ይሄም ዜጎች አቤቱታቸውን ይዘው ለመምጣት የቦታ ርቀትና የጊዜ ሁኔታ እንዲገድባቸው ማድረጉን ጠቅሰዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተያዘው የበጀት ዓመት ዜጎች በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ አቤቱታዎችን እንዲያቅርቡ የሚያስችል ስርአት ለመዘርጋት ባለፈው በጥቅምት ወር ግልጽ ጨረታ አውጥቶ ጨረታውን ያሸነፈው ተቋም ተለይቶ ስርዓቱን መዘርጋት እንደሚጀምር ገልጸዋል። በኤሌክትሮኒክስ መንገድ አቤቱታን የማቅረብ ስርአት ከሰኔ ወር 2012 ዓ.ም በኋላ ወደ ትግበራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል። ተቋሙ የሚሰጣቸው የመፍትሄ ሀሳቦች የደረሱበትን የሚከታተል የስራ ክፍል እንዳልነበረ አስታውሰው፤ ''የስራ ክፍሉ ተቋቁሞ የመፍትሔ ሀሳቦችን እየተከታተለ ይገኛል'' ብለዋል። በስራ ክፍሎች ውስጥ ያለውን የሃላፊነት መደራረብ ችግር ለመፍታት በተቋማዊ አደረጃጀቱ በድጋሚ የማዋቀር ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል። ሌላው የተቋሙ ፈተና የሚመደብለት በጀት በቂ ባለመሆኑ የሰራተኞች ፍልሰት እየገጠመው መሆኑንና መንግስት ለጉዳዩ አስፈላጊውን መፍትሔ እንዲያበጅለት ጠይቀዋል። በየክልሉ የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን አቅም ለማጠናከር የቴክኒክና የቁሳቁስ ድጋፎች የማድረግ እንዲሁም አቅማቸውን የማጎልበት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። ተቋሙ ከፖለቲካ ተጽእኖ በመላቀቁ ስራውን በነጻነት እያከናወነ በተሰጠው ሃላፊነት እስከ ከፍተኛ የመንግስት መዋቅር ያሉ ግድፈቶችን በመተቸትና የመፍትሄ ሀሳብ በማቅረብ የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዋል። ተቋሙ በአዋጁ መሰረት በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት አስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ አቅሙ እየተሻሻለ መምጣቱንና አቤቱታዎች እልባት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም እልባት የማያገኙ አቤቱታዎች ምጣኔ በፊት ከነበረበት 52 በመቶ ወደ 32 በመቶ መቀነሱን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በተሻሻለው የተቋሙ አዋጅ የመፍትሄ ሀሳቦች ምላሽና እርምጃ የማይወስዱ አስፈጻሚ አካላትን በህግ የመጠየቅ ሁኔታም መፈጠሩን አመልክተዋል። ''በአጠቃላይ ባለፉት 18 ወራት በተደረጉ የለውጥ ስራዎች የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተሻለ ተቋማዊ ቁመና ላይ ይገኛል'' ብለዋል።