የተማከለ የመረጃ አሰጣጥ ተቋማዊ አሰራር ባለመኖሩ መረጃ ማግኘት ፈተና ሆኗል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የተማከለ የመረጃ አሰጣጥ ተቋማዊ አሰራር ባለመኖሩ መረጃ ማግኘት ፈተና ሆኗል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተማከለ የመረጃ አሰጣጥ ተቋማዊ አሰራር ባለመኖሩ መገናኛ ብዙኃንና ዜጎች መረጃ ማግኘት ፈተና እንደሆነባቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ። ተቋሙ በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በመንግስት ተቋማት መገናኛ ብዙኃንና ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸው መከበሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ፣ በአሁኑ ሰዓት መረጃን ለመገናኛ ብዙሃንና ለዜጎች ግልጽና ተደራሽ ያለማድረግ ችግር እንዳለ ለኢዜአ ገልጸዋል። ''በየተቋማቱ የሚገኙ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መረጃ በወቅቱ ያለመስጠት ችግር ይታይባቸዋል'' ብለዋል። በፌዴራልና በክልል ደረጃ ለመገናኛ ብዙኃንና ዜጎች መረጃን በተማከለ መልኩ የሚያቀርብ ተቋማዊ አሰራርና ስርዓት ባለመኖሩ መረጃ ባለመስጠታቸው የመንግስትን ተጠያቂነት አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሳይፈረስ በፊት በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የህዝብ ግንኙነት ክፍሎች ተጠሪነታቸው ለጽህፈት ቤቱ እንደነበረ አውስተዋል። ሁሉም ተቋም በራሱ በሚገኘው የህዝብ ግንኙነት የስራ ክፍል መረጃ እንደሚሰጥ ገልጸው፤ አጠቃላይ የመንግስትን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ መረጃ የሚሰጥ ተቋማዊ መዋቅር እንደሌለ ጠቁመዋል። በዚህም መገናኛ ብዙሃንና ዜጎች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ሁነቶች መረጃ ሲጠይቁ ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሆነ ተናግረዋል። ''ይህም በመሆኑ ዜጎች መረጃ የመጠየቅና የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብታቸው እየተከበረላቸው አይደለም'' ብለዋል። መገናኛ ብዙኃን ለእንባ ጠባቂ ተቋም መረጃ ከማጣት ጋር በተያያዘ አቤቱታ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል። ለአብነትም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 'ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የምፈልገውን መረጃ አላገኘሁም' በሚል ባቀረበው አቤቱታ መሰረት መረጃ እንዲሰጠው መደረጉን አውስተዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን 'ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ከቤቶች ግንባታ ጋር በተያዘዘ መረጃ ጠይቄ ማግኘት አልቻልኩም' የሚል አቤቱታ ማቅረቡንም ተናግረዋል። ከዚህ በፊት መገናኛ ብዙሃን መረጃ የማግኘት ችግር በአብዛኛው የሚገጥማቸው፣ በታችኛውና መካከለኛው የአስተዳደር እርከን እንደነበር አስታውሰው፤ ችግሩ በከፍተኛ ደረጃ በሚገኙ ተቋማት እየጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል። መንግስት መገናኛ ብዙኃንና ዜጎች በተማከለ መልኩ መረጃ የሚያገኙበት ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባው ገልጸዋል። የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መረጃ መስጠት ሙያዊ ግዴታ መሆኑን ተገንዝበው አስፈላጊውን መረጃ መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም መረጃ ለመስጠት በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ መገናኛ ብዙኃን፣ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል። መገናኛ ብዙሃንና ዜጎች፣ በህገ መንግስት የተሰጣቸውን መረጃ የማግኘት መብት እንዲከበርላቸው፣ የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ዋና እንባ ጠባቂው አሳስበዋል።