ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአገራዊ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በታዛቢነት ለመሳተፍ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በማድረግ በአገራዊ ምርጫው ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ተቋሙ በዋነኛነት በህጎችና በዜጎች መብት መጠበቅ ተግባራት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል። በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነጻነት በሁሉም የመንግስት ተቋማት ውስጥ የማስተግበር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በአዋጁ መሰረት መገናኛ ብዙሃን ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ሲያደርጉ ፍትሀዊ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን የመቆጣጠር ሥራ እንደሚያከናውን አመልክተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዟዙረው ሀሳባቸውን የሚገልጹበት ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩና ተጽእኖ ስለመድረሱ አስፈላጊው ጥበቃ መደረጉን በተመለከተ ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን አስመለክቶ ያወጣቸው ህጎች በተገቢው መንገድ መከበራቸውን የመከታታል ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል። "ዜጎች በህገ መንግስቱ ምርጫን አስመልክቶ የተሰጧቸው መብቶች እየተከበሩ መሆናቸውን የመቆጣጠር ተግባር ተቋሙ ያከናውናል" ብለዋል። ተቋሙ ይህን ስራ ለማከናወን ያስችለው ዘንድ የእቅድ ዝግጅት ሰነድ ማዘጋጀቱን ዶክተር እንዳለ ገልጸዋል። እንደ ዋና እንባ ጠባቂው ገለጻ፤ ተቋሙ በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርገው የመገናኛ ብዙሃንን ሥራ መቆጣጠር ላይ ነው። ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም የምርጫ ቅስቀሳው ሥራ ሲጀመር ተቋሙ ወደ ተግባራዊ ሥራ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከዚህ በፊት በተካሄዱት አገራዊ ምርጫዎች የፖለቲካ ሁኔታው ለመታዘብ ስላልጋበዘው ተሳትፎ እንዳላደረገ ያስታወሱት ዶክተር እንዳለ፤ ተቋሙ አምስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ቢጠይቅም ''አያገባህም' መባሉን ተናግረዋል። በነበረው ተጽእኖ ምክንያት በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረትም በአገራዊ ምርጫዎቹ ምንም አይነት ቁጥጥር ማድረግ እንዳልቻለም ጠቅሰዋል። አሁን በአገሪቱ ባለው አንጻራዊ የተሻለ ሁኔታ ተቋሙ በምርጫው ላይ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት አስፈላጊውን ተሳትፎ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። ታዛቢነትን ጨምሮ ተቋሙ በምርጫው ላይ ስለሚኖረው ተሳትፎ በቀጣዮቹ ሳምንታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ምክክር እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም