ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ-ክርስትያን በቦንብ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች 200 ሺህ ብር ሰጠች

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ-ክርስትያን በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተፈፀመው የቦንብ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የሚውል የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገች። የድጋፍ ገንዘቡን የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ተቀብለዋል። የቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ መሪዎች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝተው በጥቃቱ የተጎዱትን ዜጎች የጎበኙ ሲሆን አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል። የተፈጸመው ጥቃት ከማንኛውም የሰው ፍጡር የማይጠበቅና ሊወገዝ የሚገባው ነው ሲሉ የቤተ ክርስትያኗ ፕሬዚዳንት ፓስተር ይልማ ዋቄ አመልክተዋል። ህይወታቸው ላለፉ ዜጎች መንግስተ ሰማያትን፤ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን፤ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ደግሞ ማገገምን ተመኝተዋል። ቤተ-ክርስቲያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሩትን የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ጥሪ እንደምትደግፍ የገለፁ ሲሆን  በሀገሪቱ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩም ቤተ-ክርስቲያኗ ለተከታዮቿ ሰላምንና ፍቅርን መስበኳን ትቀጥላለች ተብሏል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በዚሁ ጊዜ ቤተ-ክርስቲያኗ ላደረገችው ሰብዓዊ ድጋፍ በተጎዱ ቤተሰቦች ስም አመስግነዋል። በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ የእርዳታ ድጋፉን የማስተባበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በግለሰቦች የሚደረጉ ድጋፎች እንዳይባክኑም በከተማ አስተዳደሩ በኩል እንዲሆን ለህብረተሰቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም