ቀጥታ፡

የማህጸን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አለመከናወናቸው ስርጭቱ እንዲጨምር አድርጎታል

አዲስአበባ፣ የካቲት 12 /2012 (ኢዜአ) በኢትየዽያ የማህጸን ጫፍ ካንሰር በየአመቱ ከ5ሺህ በላይ ሴቶችን ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳርግ ታውቋል። ሌሎች ከ7ሺህ በላይ ህሙማን ደግሞ በበሽታው እንደሚያዙ ነው የተነገረው። የማህጸን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል እና የህክምና መንገዶች ላይ ምርምር ለማድረግ የተቋቋመው የዘርፉ ተመራማሪዎች ካውንስል፣ ሁለተኛውን የምክክር መድረክ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት እየተካሔደ ይገኛል። መድረኩ በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ዋና አዘጋጅነት የሚካሔድ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር አካላት ተሳትፈውበታል። በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ5ሺህ በላይ ሴቶች  በየአመቱ በማህጸን ጫፍ ካንሰር ምክንያት ህይወታቸው ሲያልፍ ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በበሽታው ይያዛሉ፡፡ በሽታው ይዟቸው ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በሗላ ታማሚዎቹ ወደ ሕክምና ጣቢያ መምጣታቸው ደግሞ የበሽታውን አስከፊነት እንዳሳደገውም  ተገልጿል፡፡ የግንዛቤ ማነስ፣ ዘርፉ ላይ የሚታየው የህክምና እጥረት እንዲሁም ለምርምር ስራዎች በቂ ድጋፍ አለመኖር በሽታውን በሚፈለገው ልክ መከላከል እንዳይቻል ካደረጉት ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን የገለጹት በአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ30 አመታት በላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ይርጉ ገብረሕይወት ናቸው። ዶክተር ይርጉ እንደገለጹት የማህጻን ጫፍ ካንሰር እያስከተለ ያለውን ጉዳት በተሟላ መረጃ ለማወቅ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ፣ በተለይም የማህጸን ጫፍ ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ጉዳት እያስከተለ አንደመሆኑ መጠን ሰፊ የሆኑ ተግባራዊ ስራዎች ያስፈልጉታል ብለዋል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣ ጠንካራ የሆነ የህክምና ማዕከላት ግንባታ በቅድሚያ ሊከናወኑ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል እንደሆኑ ዶክተር ይርጉ አስረድተዋል። በሌላ በኩል የማህጸን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከልና በዘርፉ ላይ ለሚካሄደው ምርምር የሚውል 4ሚሊዮን ብር መመደቡን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ናቸው፡፡ ለበሽታው መከሰት ምክንያት የሆኑትን የቫይረስ አይንቶች ለመለየት፣ ለአገሪቱ ተስማሚ የሆኑ የህክምና መንገዶቹን ለመመረጥ፣ በተጨማሪም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች መስጠት  የምርምር ስራዎቹ የሚያካትቷቸው ነጥቦች ናቸው ብለዋል፡፡ ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ 14 አመት ለሞላቸው ልጅ አገረዶች የማህጸን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የማህጸን ጫፍ ካንሰር በአፍሪካ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ሁለተኛው የካንሰር አይነት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም