የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የፈተናዎች ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

87
አዲስ አበባ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ)  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የፈተናዎች ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አገር አቀፍ የትምህርት ምዝናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም የ12ኛ እና የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ እና ክልላዊ ፈተናዎች የሚካሄዱበትን ቀን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የአገር አቀፍ የትምህርት ምዝና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ረዲ ሽፋ እንደገለጹት የአገር አቀፍ ፈተና ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ነው። የ12ኛ ክፍል ፈተናዎችን ሙሉ ለሙሉ በኤጀንሲው የሚያዘጋጅ  ቢሆንም የ8ኛ ክፍል ፈተና ግን በክልሎች ዝግጅቱ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። ቀድሞ ይሰጥ የነበረው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሰረት መቅረቱ ፤ በዘንድሮው  ዓመት ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በቂ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና  የዩኒቨርሲቲ መግቢያ  እንደመሆኑ መጠን ፤ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አንድ ላይ በመሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ሲካሄድ መቆየቱን አሰታውሰዋል። ይህ ሁኔታ በዘንድሮው ዓመት ተቀይሮ የፈተናዎች ዝግጅት እና አስተዳደር ላይ የሚሰራው ኤጀንሲው በመሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና የማዘጋጀት ተግባሩን  እያጠናቀቀ እንደሆነ ተናግረዋል። ተቋሙ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሑራንና ከእያንዳንዱ ትምህርት ዘርፍ ሙያተኞች ጋር በቅንጀት በመሥራት ፈተናው እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል። በቀጣይም የቀሩትን ጥቂት ሥራዎች በማጠናቀቅ፤ ፈተናዎቹን በህትመት የማዘጋጀቱ ሥራ ለአታሚዎች ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የፈተና ህትመት ስራውን በአብዛኛው ብርሃንና ስላም ማተሚያ ድርጅት ይሰራ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ዓመት ግን ጨረታውን ለሁሉም አታሚ  ድርጅቶች ግልጽ በማድረግ ለሚያሸንፈው አካል በመስጠት በጥንቃቄና ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ እንዲታተም ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል። ቀደም ሲል በወረቀት ሲካሄድ የቆየው የፈተና ምዝገባ በአዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ በኦንላይን መካሄዱን ገልፀዋል። በዚሁ መሰረት በክልሎችም ምዝገባውን በኦንላይን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በምዝገባም ሆነ በፈተናው ወቅት እንዲሁም ከፈተናው በኋላ ውጤት አሰጣጡ ላይ የተለያዩ ችግሮች እንዳይኖሩ ከወዲሁ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም