ቀጥታ፡

በአሶሳ ከተማ በዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ 16 ሰዎች ተያዙ

አሶሳ (ኢዜአ) የካቲት 12/2012 በአሶሳ ከተማ በምሽት የዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ 16 ባጃጆች ከእነ አሽከርካሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የከተማው ፖሊስ ፅሀፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በፅሀፈት ቤቱ የወንጀል መከላከል ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ኢንስፔክተር ደረጃ ኢታና እንደገለፁት በከተማው የሚፈፀም የዘረፋና ስርቆት ወንጀል እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ችግሩን ለማስቆም ፖሊስና ህብረተሰቡን ያቀፈ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከየካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡ ግብረ ኃይሉ ከህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ እስከ አሁን ድረስ 16 ባጀጆችን ከእነ አሽከርካሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስረድተዋል፡፡ አሽከርካሪዎቹ በእኩለ ለሊት እየተዘዋወሩ ዘረፋ ለሚፈፅሙ ግለሰቦች የትራንስፖርት አገልግሎቱን በመስጠት ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው ብለዋል። ካናቢስ የተባለ አደንዛዝ እፅ በማዘዋወር የተጠረጠሩ ሌሎች ስምንት ግለሰቦችንም ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ሥራ እንዲውሉ አድርጓል ። በቁጥጥር ስር በዋሉ ግለሰቦች ላይ የሚደረገው ምርመራ እንደተጠናቀቀ ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል ተብሏል ። የግብረ ኃይሉ ዓላማ የዘረፋና ስርቆት ወንጀሎችን በዘላቂነት በማስወገድ የነዋሪውን ደህንነት ማስቀጠል ነው ያሉት ኢንስፔክተር ደረጀ የከተማው ነዋሪም ከግብረ ሃይሉ ጎን በመቆም ተሳትፎውን እንዲያጠናከር ጥሪ አቅርበዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም