ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን የአንድ ዓመት ሪፖርትን አዳመጡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን የአንድ ዓመት ሪፖርትን አዳመጡ
አዲስ አበባ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን የአንድ ዓመት ሪፖርትን አዳመጡ። የኮሚሽኑን የአንድ ዓመት ጉዞ የሚገልጽ ሪፖርት ያቀረቡት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳትና የኢትዮጵያ ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ስራውን ለማቀላጠፍ አምስት የተለያዩ ኮሚቴዎችን አደራጅቷል። የተደራጁት ኮሚቴዎች እውነትን ለማፈላለግ መረጃ የሚያሰባስብ፣ በደል የደረሰበትን ሰው የሚያሰባስብና ስልጠና በመስጠት ግንዛቤ እንዲፈጠር የሚያችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ ስለ ኮሚሽኑ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። በዚህም የኮሚሽኑን ዓላማ እና አስፈላጊነት ለማስገንዘብ ከተለያዩ አካላት ጋር የውይይት መድረክ መመቻቸቱን ገልጸዋል። ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ስልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል። ኮሚሽኑ አዋጁን በብቃት ማስፈጸም እንዲችል የሚያግዝና የተለያዩ ጉዳዮችን ለመመርመርና ለማዳመጥ የሚያስችል ደንብ እንዲወጣ ሰብሳቢው ጠይቀዋል። የእርቀ ሰላም ኮሚሽን የተቋቋመው በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዪ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ሌላው ኮሚሽኑ እንዲቋቋም መሰረት የሆነው ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍና አሕጉራዊ ስምምነቶች የተረጋገጡትን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ እና ተግባራዊ ለማድረግ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ጉልህ የመብት ጥሰቶችን ምንነት በግልጽ መለየት አስፈላጊ ስለሆነ እና ለእርቀ ሰላሙም አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ነው።
በተለያዩ ጊዜና የታሪክ አጋጣሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሌላ በደል ተጠቂዎች የሆኑ ወይም ተጠቂዎች ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች በደላቸውን የሚናገሩበትና በደል ያደረሱ ዜጎች ላደረሱት በደል በግልፅ በማዉጣት የሚፀፀቱበት እና ይቅርታ የሚጠይቁበት መንገድ በማበጀት እና እርቀ ሰላም በማዉረድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ተቋቁሟል። ኮሚሽኑ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ እየፈረሰ የሚሰራ ሳይሆን እየተገነባ የሚሄድ ስርዓት ለመፍጠር፣ ዲሞክራሲያዊ ሀገርና ማህበረሰብ ለመገንባት ሰፊና ተቀባይነት ያለው የእውነትና፣ የእርቅ እና የሰላም ዓላማ ያነገበ ነው። ለግጭትና ቁርሾ ምክንያት የሆኑትን ዝንፈቶች ምክንያቶችና የስፋት መጠን አጣርቶ እውነታውን በማዉጣት ተመልሰው እንዳይመጡ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችንም ይወስዳል። እነዚህ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያመነጭ ገለልተኛ እና ነጻ ኮሚሽን ማቋቋም በማስፈለጉ ኮሚሽኑ መቋቋሙ በአዋጁ መጠቀሱ ይታወቃል።